እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

፯ - “ከክፉ ሰውረን እንጂ”

    ፯ - “ከክፉ ሰውረን እንጂ”

ለአባታችን የምናቀርበውን የመጨረሻ ልመናም በኢየሱስ ጸሎት ውስጥ ተጠቃልሎ ይገኛል፡፡ ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም፡፡ ቃሉ እያንዳዳችንን በግል የሚካ አባባል ነው፤ ዳሩ ግን መላው የሰው ልጅ ቤተሰብ ይድን ዘንድ ከመላዋ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር የምንጸልየው “እኛ” ነን፡፡ የጌታ ጸሎት በማያቋርጥ መልኩ ወደ ተለያዩት የእግዚአብሔር የድኀነት ዕቅድ አቅጣጫዎች ይመራናል፡፡ በኃጢአትና በሞት ትዕይንት ውስጥ ያለው የእኛ ትስስር “የቅዱሳን ሱታፌ” ወደሆነውና በክርስቶስ ሥጋ ወደሚገለጸው አንድነት ይለወጣል፡፡

በዚህ ልመና መሠረት ክፋት ረቂቅ ነገር አይደለም፤ ነገር ግን አንድ አካልን፣ ሰይጣንን፣ ክፉውን፣ እግዚአብሔርን የሚቃወመውን መልአክን ይመለከታል፡፡ ሰይጣን ከእግዚአብሔር እቅድና በክርስቶስ ከሚፈጸመው የድኅንነት ሥራው ፊት “ራሱን የሚጥለው /መሰናክል የሚሆነው/” ነው፡፡

“ሰይጣን ከመጀመሪያውም ነፍሰ ገዳይ … ሐሰተኛና ከሐሰት አባት” “ዓለምን ሁሉ የሚያስተው” ነው፡፡ ዮሐ 8፡44፣ ራእ 12፡9  በእርሱ ምክንያት ኃጢአትና ሞት ወደ ዓለም ገቡ፡፡ “ምርሱ በማያዳግም ሁኔታ ድል በመሆኑም ፍጥረት ሁሉ “ኃጢአትና ሞት ከሚያስከትሉት ጥፋት” ነፃ ይወጣል፡፡ አሁን “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው እራሱን እንዲጠብቅ ክፉም እንዳይነካው እናውቃለን፡፡ የእግዚአብሔር እንደሆንን ዓለምንም በሞላው በክፉ እንደተያዘ እናውቃለን፡፡” 1ዮሐ 5፡18-19

ኃጢአታችሁ ይደመሰስላችሁና ይቅርታ ያደረገላችሁ ጌታ ወደ ኃጢአት መምሪት የለመደው ባለጋራ እንደያስደነግጣችሁ ከጠላታችሁ ከዲያቢሎስ ሽፍጦች ይከላከልላችኋል፣ ይቀብቃችኋልም፡፡ ራሱን በእግዚአብሔር የሚሰጥ ሰው ዲያቢሎስን አይፈራም፡፡ በእውነትም “እግዚአብሔር የእኛ ከሆነ ከቶ የሚቃወመን ማነው?”

ኢየሱስ ሕይወቱን ስለእኛ ይሰጥ ዘንድ በገዛ ፍቃዱ ራሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠበት ሰዓት “በዚሁ ዓለም ገዥ ላይ” የማያዳግም ድል ተገኘ፡፡ የዚህ አለም ፍርድ ይህ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ገዥም “ወደ ውጭ ይጣላል” ዮሐ 12፡31፤ ራእ 12፡11 እርሱ “ሴቲቱን ቢያሳድዳትም” ራእ 12፡13-16 እርሷ በመንፈስ ቅዱስ “ጸጋ የተሞላች” እና በመንፈስ ቅዱስ ከኃጢአትና ከሞት ጥፋት የተጠበቀች /ያለ አዳም ኃጢአት የተጸነሰች፣ እጅግ የተቀደሰች፣ የአምላክ እናት፣ ሁልጊዜ ድንግል እና ወደ ሰማይ የተወሰደች/ አዲሲቷ ሔዋን ስለሆነች ሊይዛት አይቻለም፡፡ “ዘንዶውሙ በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ ከእርሷ ዘር የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፡፡” ራእ 12፡17 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስና ቤተ ክርስቲያን “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ና!” እያሉ ይጸልያሉ፤ የእርሱም መመጣት ከክፉው ያድነናልና፡፡

ከክፉው ለመዳን በምንለምነበት ጊዜ ባለቤታቸውና አነሳሻቸው እርሱ ከሆነ ካለፉት፤ ካሁንና ከወደፊት ክፋቶች ነፃ እንሆን ዘንድም እንፀልያለን፡፡ ቤተክርስቲያን በዚሁ በመጨረሻው ልመና የአለምን ችግር ሁሉ በአብ ፊት ታቀርባለች፡፡ እርሷ የሰውን ልጅ ከከበቡት ክፋቶች ነፃ ለማውጣት እንዲሁም እጅግ የከበረውን የሰላም ስጦታና የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ትእግስት በሞላበት ተስፋ የምንጠባበቅበትን ጸጋ ለማግኘት ትጸልያለች፡፡ በዚህ አይነት በመጸለይ ቤተክርስቲያን “የሞትና የሲኦል መክፈቻ” ባለቤት በሆነው “ባለውና በነበረው በሚመጣውም ሁሉንም በሚገዛ ጌታ አምላክ” በእምነት በትህትና የሁሉንም ሰውና የሁሉንም ነገር በአንድነት መሰባሰብ ትጠብቃለች፡፡

ጌታ ሆይ ከክፉ ሁሉ እንድታድነን እንለምንሃለን፤ በዘመናችን ሰላምን ስጠን፡፡ በምህረትህ በመታገዝ የተቀደሰውን ተስፋና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት በመጠባበቅ፣ ሁልጊዜ ከኃጢአት ነፃ እንድንሆንና ከጭንቀትም እንድንጠበቅ አድርገን፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት