እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ቅድስት ማሪያ ጎሬቲ ምን ታስተምረናለች?

የማንኛውም ሰው ሕይወት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሚያስተምረን ነገር አለ፤ አንድም ጥሩ አብነትን እየሰጠ በአዎንታዊ ሁኔታ ሲሆን ወይም ደግሞ ጥሩ ያልሆነ አናኗር በመኖር የመጥፎ ሕይወትን አስከፊ ገጽታ በተግባር እያሳየን ከዚያ መሰል ሕይወት እንርቅ ዘንድ በአሉታዊ መልኩ ያስተምረናል። ይበልጡን ደግሞ የተፈጠሩበትን ዓላማ እንደሚገባ ኖረው ሕያው ከሆነውና ሕያው ከሚያደርገው የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ጉያ እቅፍ ውስጥ ለመሆን ወደ ሰማያዊው እልፍኝ የተሻገሩ ቅዱሳንና ቅዱሳት ደግሞ ላቅ ያለና ለዘለዓለማዊነት የሚያበቃንን ትምህርርን ያስተላልፉልናል፤ አንዳንዶቹም የምድራዊ ሕይወታቸውን እስካለማደራደር ድረስ! በዚህ ሃሳብ ለዘመናችን ጥሩ አብነት ትሆናለች ብለን ያሰብናት ቅድስት ማሪያ ጎሬቲ ናት፤ ከርሷ ሕይወት የምንማረውን አንባቢው ታሪኳን ካነበበ በኋላ በአስተንትኖና በጸሎት መንፈስ ሆኖ ለራሱ ቁም ነገሮችን ይቃርም ዘንድ በማለት የሕይወት ታሪኳን በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 ማሪያ ጎሬቲ በሰሜናዊው ምሥራቅ ጣልያን ተራራማ መንደር ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1890 ዓ.ም. ተወለደች። ድኻ አርሶ አደሮች  ወላጆቿ አቶ ሉይጂና ወ/ሮ አሱንታ ካፈሯቸው ስድስት ልጆች ውስጥ ሁለተኛዪቱ ናት።

እ.ኤ.አ. በ1896 ዓ.ም. ሻል ያለ ኑሮና የበለጠ ለም መሬት ማግኘትን ተስፋ በማድረግ ቤተሰቡ በሙሉ ከትውልድ ቀዬያቸው ወደ ደቡብ ምእራብ የአገሪቱ ክፍል በመሄድ ፌሪየሬ ዲ ኮንካ በሚባል ስፍራ ሰፈሩ። በዚያም በአንድ የባለሃብት መሬት ላይ የሚገኝ ቤትን ከአንድ ልጁ ጋር ብቻ ይኖር ከነበረውን ጆቫኒ ሴሬኔሊ ከሚባል ሰው ጋር በዚያ መሬት እየሠሩ ለመኖር ቤትን ተጋሩ።

በርግጥ ሉይጂ አሁን የሚሠራበት መሬት በጣም ለም ነው፤ ሆኖም ግን ለእሱ ጉዳቱ ያመዘነ ሆነበት። ይህ መሬት ዙሪያው የወባ ትንኝ እጅጉን የሚገኝበት አረንቋ የከበበው ነው። በዚያን ዘመን በደቡብ ጣልያን ለሚኖሩ ሰዎች የወባ በሽታ ከወረርሽኝ በማይተናነስ መልኩ ተሰራጭቶ ነበር። የ20ኛው ክ.ዘ. መባቻ ላይ የወባ በሽታን የመግታት ግብግቡ ውጤታማ ቢሆንም ለሉይጂ ጎሬቲ ግን ይህ በጣም የዘገየ ነበር፤ እርሱ በዚሁ በሽታ እ.ኤ.አ. በ1900 ዓ.ም. ከዚህች ዓለም በሥጋው አልፏል። በመሞት ላይ እያለም ልጆቻቸውን ይዛ ወደ ትውልድ መንደራቸው ይመለሱ ዘንድ ሚስቱን አደራ ብሏት ነበር ባይተገበርም።

አሱንታ ከባሏ ሞት በኋላ በእርሻ ውስጥ የእርሱን ሥራ ቀጠለች። በዚህ ወቅት አሥር ዓመት እድሜ የነበራት ማሪያ የቤት ውስጥ የሥራ ጫናና ልጆችን የመንከባከብ ኀላፊነትን በገሃድ ተረከበች። ይህንን ሸክም በሚያስገርም ብስለትና ብቃት መወጣቱን ተያያዘችው፤ ማሪያ ላያት ሁሉ የምትወደድ ዓይነት ልጅ ነበረች፤ ማሪያ ደግ፣ የደስ ደስ ያላትና ፍልቅልቅ ልጅ ነበረች። የእያንዳንዷ ቀን ውሎዋ የግል ነገሯን የማታስቀድምበትና የመስዋእትነት ነበር፤ ለዚህም የሚሆናትን ኃይል በትጋት ከምታደረሰው ጸሎቷ ታገኝ ነበር።

በከባድ ድኽነት ውስጥ ሆና በተጨማሪም የትላልቅ ሰዎችን የቤት ውስጥ ኀላፊነት በልጅነት እድሜዋ መሸከሟ ማሪያን ተስፋ አላስቆረጣትም ነበር፤ ሆኖም ግን  እ.ኤ.አ. ከ1901 ዓ.ም. ጀምሮ በሕይወት መንገዷ የፍርሃትና የኀዘን ግርዶሽ አጠላበት። አሌሳንድሮ የተባለው  ከአባቷ ጋር ቤትን ተጋርቶ የነበረው ሰው ልጅ ወጣት ጎረምሳ ማሪያን ለብቻዋ ባገኘበት አጋጣሚ ሁሉ ወሲባዊ ጥቃት ሊሰነዝርባት ማድባት ጀመረ። በተደጋጋሚ በሃሳቡ ያለመስማማቷ አበሳጭቶት ድርጊቱን ለአንድ ሰው እንኳ ከተናገረች እንደሚገድላት ዛተባት። ይህንንም ከነገራት በኋላ ከነበረው ማሪያን የመከታተል ሁኔታ ለዘብ ያለ መሰለ።

እ.ኤ.አ. ሰኔ 16 ቀን 1902 ዓ.ም. የመጀመሪያ ቅዱስ ቁርባኗን የተቀበለችበት ቀን ለማሪያ ከትልቅ ደስታ ቀኖቿ አንደኛው ነበር፤  እግዚአብሔርን ከነገሮች ሁሉ በላይ ለማፍቀር በውስጧም የጸናችበት ወቅት ነበር። ከዚህ በኋላ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማለትም ሐምሌ 5 ቀን ከእርስዋ በቀር የቤተሰቦቿ አባላት በሙሉ እህል የሚወቃበት እለት በመሆኑ ወደ ማሳ ሄደው ነበር፤ ይህ ሁኔታ ለአሌሳንድሮ የቆየ እኩይ ምኞቱን ለመፈጸም ምቹ አጋጣሚ ነው ብሎ እንዲያስብ አደረገው፤ ስለዚህም ወደነማሪያ ቤት በመሄድ ማሪያን አጠመዳት። የያዘውንም ጩቤ እያሳያት በመዛት አስገድዶ እኩይ ምኞቱን ሊፈጽምባት ዳግም አስፈራራት፤ ማሪያ ግን በሙሉ ኃይሏ እየተቃወመችው «አይሆንም! ይህ ኃጢአት ነው! እግዚአብሔር አይፈልገውም! ወደ ገሃነም ትወርዳለህ!» ብላ ጮኸችበት። ምኞቱ አልሰመረለትምና አሌሳንድሮም እጅግ ተበሳጨ፤ በያዘውም ጩቤ በሚዘገንን ሀኔታ ማሪያን አሥራ አራት ጊዜ ወጋት፤ ከዚያም ሌላ ክፍል ውስጥ በመግባት በሩን ቆልፎ ተደበቀ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማሪያ በወለል ላይ ራሷን ስታ ተዘርራ የአሌሳንድሮ አባት ሴሬኔሊ አገኛት። በፈረስ በሚጎተት የወቅቱ አምቡላንስ /የአደጋ ጊዜ ሰው ማመላለሻ/ ማሪያ ወደ ሆስፒታል እንድትወሰድ ተደረገ። ማሪያ በማግስቱ በሆስፒታል አረፈች፤ ሆኖም ግን ላናዘዟት ካህን አሌሳንድሮን ይቅር እንዳለቸውና በመንግሥተ ሰማይም እንደሚገናኙ ተስፋዋ እንደሆነ ነገረቻቸው።

ማሪያ ጎሬቲ ስትሞት የ12 ዓመት ልጅ ስትሆን፤ አሌሳንድሮ ይህን ወንጀል ሲፈጽም እድሜው 20 ዓመት ነበር። በዚህ ጥፋቱ 30 ዓመት እስር ቤት እንዲያሳልፍ ተፈረደበት። የተወሰኑ ዓመታት እስኪያልፉ ድረስ አሌሳንድሮ ባደረገው ወንጀል አልተጸጸተም ነበር፤ ነገር ግን በአንድ ወቅት ማሪያ ተገልጻለት አበባ ስታበረክትለትና የይቅርታ ቃሏንም ስትደግምለት ይህ ለጸጸቱ ምክንያት ሆነው። እ.ኤ.አ. በ1929 ዓ.ም. አሌሳንድሮ ቅጣቱን ጨርሶ ከእስር ቤት ሲወጣ ወደ ማሪያ እናት ወደ አሱንታ ጎሬቲ በመሄድ ልጇ ላይ ላደረሰው በደል ይቅርታ ጠይቋል። እ.ኤ.አ. ሰኔ 24 ቀን 1950 ዓ.ም. የማሪያ ጎሬቲ ቅድስና ሲታወጅ አሌሳንድሮና አሱንታ በአንድ ላይ ተገኝተው ነበር። አሌሳንድሮ እስከ ሞተበት 1969 ዓ.ም. ድረስ በፍራቼስኮሳውያን ካፑቺን ገዳም አትክልት ሠራተኛ በመሆን የተቀረ ሕይወቱን አሳልፏል።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት