እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የበደለኝን ይቅር ብዬ እንዳልፈው

የበደለኝን ይቅር ብዬ እንዳልፈው              (በብሥራተ ገብርኤል)

የአፈጣጠራችንና የተክለ ሰውነታችን ጉዳይ ሆኖ እጆቻችንን ወደ ፈጣሪ አቤት ለማለት ስናነሣ እግረ መንገዱን ወደ ጎን ወደ ወንድሞቻችን መዘርጋቱ ግድ ነው። ጌታችን ያስተማረን ጸሎት የሚለውም “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፤ በደላችንን ይቅር በለን” ነው። ጸሎቱንም “አባታችን” ሆይ ብለን በመጀመራችን እርስ በርሳችንን ወንድማቾችና እህትማማቾች ያደርገናል። ስለዚህ ምሕረቱን ከእርሱ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታው፤ እኛን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከበደሉን ጋር ሰላም መፍጠር ነው። በስብከተ ወንጌሉም ያስገነዘበን “ለራስ መባ ከማቅረብ በፊት ከባላጋራችን ጋር መታረቅ” እንዳለብን ነው። በዚህ ምክንያት መስዋዕተ ቅዳሴ ለፈጣሪያችንም ስናቀርብ ኅብስቱንና ወይኑን ወደ ቅዱስ ሥጋውና ደሙ እንዲቀይረው ከመጸለያችን በፊት ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “በተቀደሰ አሳሳም እርስበርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ” ብሎ እንደመከረው እርስ በርስ ሰላምታ እየተሰጣጣን ይቅር መባባል ይጠበቅብናል። ጌታችን ስለ ስርየተ ኃጢአት ሲያስተምረን “ለጸሎት በቆማችሁ ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት” እንዳለ እንገነዘባለን።

ከዚህም በተጨማሪ አጋጣሚ በተገኘ ቁጥር ሁሉ ሌሎችን ይቅር ማለት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። አለበለዚያ ኢየሱስ የነገረን ምሳሌ ንጉሡ የባለሟሉን ዕዳ ሙሉ በሙሉ ሲሰርዝለት እርሱ በፈታው እዳ ያለበትን ባልንጀራውን በማስቃየቱ የደረሰበት በኛ ላይ ሊፈጸም እንደሚችል “እንግዲህ እያንዳችሁ ወንድማችሁን ይቅር ባትሉ በሰማይ ያለው አባቴም እንዲሁ ያደርግባችኋል” በማለት አስጠንቅቆናል።

በዓለም ዙርያ አብረን ስንኖር ያለውን ውሱን የማቴርያል፣ የጊዜ፣ የጉልበት . . . ወዘተ ምጣኔ ሃብት በጋር እንቋደሳለንና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ግጭት መከሰቱ አይቀሬ ነው። ነገር ግን ገና ከኦሪት አንስቶ እግዚአብሔር ለራሱ የመረጠውን ሕዝብ የሚተዳደርበት ሕግ በሙሴ አማካይነት ሲደነግግ “በማንም ላይ ቂም አትያዝ፣ በእርሱ ምክንያት በደል እንዳትፈጽም ከእርሱ ጋር ያለህን አለመግባባት በስምምነት አስወግድ” ነው ያለው።

ሁሉን ታግሰን ለማለፍ በሞከርን ቁጥር አጅሬ መፋቀራችንን አይወድምና በሰበብ አስባቡ እንድንናቆር ይፈታተነናል። በአንዴ ብቻ አያቆምም፤ በተደጋጋሚ። ኢየሱስ የቅዱስ ጴጥሮስን “ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ግዜ ልማረው?” ጥያቄ “ሰባ ጊዜ ሰባት” ብሎ በመመለሱ ትንሽም ትልቅም በደል በደረሰብን ቁጥር የቂም ማሕደራችን ከኮሮጆ ወጥተን እየመዘገብን በሒሳብ መደመርያ እንድናሰላው ሳይሆን በተቻለ አጋጣሚ ሁሉ ምሕረት እንድናደርግ ነው። “በሰይጣንን እንዳንታለልም፤ እርስ በርስ ይቅር መባባል እንዳለብን” ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናል። ምክንያቱም በሩቅ በሰማይ ለሚኖረው እግዚአብሔር ያለንን ፍቅር መግለጽ የምንችለው በቅርባችን የሚገኙትን የእርሱ ፍጡራን በማፍቀር ብቻ ነው። ያለበለዚያማ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ያላየውን እግዚአብሔር እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው።”  በማለት ይወቅሰናል። የሙሴ ሕግ መምህር ወደ ኢየሱስ ቀርቦ ከሁሉ የሚበልጠው የመጀመርያው ትእዛዝ የትኛው ነው ብሎ ሲጠይቀው ፈጣሪ አምላክህን መውደድ መውደድ መሆኑን ከመለሰለት በኋላ በማስከተል አይነጣጠልምና፤ ባልንጀራን መውደድ ያልተናነሰ ሁለተኛ ትእዛዝ መሆኑን ገልጾለታል።

አንዳንድ ጊዜም በተለያዩ ነገሮች ህሊናችን እየሻከረ፣ ትንሿም ኣንከን ጎልታ እየታየችን፣ የተመኘነው ሳይሳካ ሲቀር ሌሎችን ለመወንጀል እንነሳለን። ለምሳኤ ያህል፤ የትምህርት ቤት ፈተና ውጤቱ ያማረ ከሆነ “A” አገኘሁ ስንል፤ ያልተሳካ ጊዜ ግን “F” ሰጠኝ ብለን ኃላፊነቱን ወደሌላው እናሸጋግራለን። አመልካች ጣታችንን በሌላ ሰው ላይ በቀሰርን ቁጥር ሌሎቹ ሦስት ጣቶች የሚያመለክቱት ወደኛው መሆኑን እናስተውል። አውራ ጣታችን ደግሞ ከላይ ሆኖ የሚያየን ሁሉ ፈራጅ ወደሆነው የሠራዊት ጌታ ነው።

ይቅር መባባሉ ጠቀሜታው የጋርዮሽ ነው። ለተበዳይ በልቡ እያመረቀዘ ያለውን የጥላቻ መንፈስ ሲያሽቀነጥርለት ለበዳይ ደግሞ ሰላምን ይሰጣል። ዘወትር የሚፈሰውን የእግዚአብሔርን ፀጋ እንዲጠቀመበት ያስችለዋል። ጣራ ቀደው ያመጡለትን በሽተኛ ኢየሱስ እጅና እግሩ ካሰረው ደዌ ከማላቀቁ በፊት አምላኩን በመበደል ለሰራቸው ስህተቶች ይቅር አለው። ይህን በማድረጉም ይቅርታ ታላቅ የደኅንነታችን ሚስጥር እንደሆነ አስተማረን። ምክንያቱም ሙሉ አካል ኖሮት፤ ዘላለማዊ ሕይወትን ካላገኘ ፋይዳ አይኖረውም።

ጥፋት የሠራ ሰው በጥፋቱ ተሸማቆ ሳለ የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ ልንቀየመው ወይንም ልንቀበለው ብንነሳ በእርጥብ ቁስል እንጨት እንደመስደድ ይቆጠራል። ነገር ግን ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚያስተምረን “እኔ የምደግፈውና የመረጥኩት በእርሱም ደስ የሚለኝ አገልጋዬ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን እንኳን አይሰብርም።” እኛም ነገ አጥፍተን ምሕረትን ፈላጊ እንሆናለን ወይንም ከዚህ ቀደም ምሕረትን አግኝተናንልና ለመቀበል ከመነሳት በፊት “በሰፈርንበት ቁና መሰፈራችን” አይቀሬ መሆኑን በማሰብ “ሰዎች ሊያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም እንዲሁ ማድረግ እንደሚኖርብን” ከአዳኛችን ትምህርት መረዳት ይኖርብናል።

ይቅር ለመባባል ፈቃዱም ኖሮን ብዙ ጊዘ የሚቃጠለውና ይህንን ፀጋ ሳንጠቅመቨት የሚቀረው ማን እንዳጠፋ ስንመረመር፣ ያጠፋ ቀድሞ ይቅርታ ይጠይቅ ስንባባል  ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ግን በተደጋጋሜ የሚያስተምረን በጎ ለመስራት መሽቀዳደም እንዳለብን፤ “ክርስቶስ ይቅር እንዳለን ይቅር እንድንባባል” ነው። ክርስቲያንነታችንንም የምንመስከረው አስፈላጊ ከሆን ተበዳይ እኛ ሆነን ሳለን ይቅርታ ጠያቂዎችም ሆነን ስንገኝ ነው። በተራራው ስብከቱ ላይ “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አለው? ኃጢአተኞችስ ይህንን ያደረጉ የለምን?” ባንጻሩ ግን “የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ” ይለናል።

ዮሴፍ የገዛ ወንድሞቹ ለብሱ ገፈው ለባርነት ሸጠውት ነበር። ነገር ግን በሀገራቸው ድርቅ ገብቶ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው እጁ ላይ በወደቁ ጊዜ ከመቀበል ይልቅ ያለምንም ክፍያ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እህል ሰጣቸው።

ንጉሥ ሳዖል ክፉ መንፈስ እየተጠናወተው ታማኝ አገልጋዩን ዳዊትን ብዙ ጊዜ ለመግደል ይነሣሣ ነበር። በተደጋጋሚ ጦር አዝምቶበታል። ነገር ግን ሳዖል በእጁ በገባ ጊዜ ዳዊት ጠላቱን ከማጥፋት ታቅቧል።

ትንሽም ትልቅም ክፉ ሥራ የሠሩብንን ሰዎች ይቅር ማለት ከባድ መስሎ ሊታየን ይችላል። ኢየሱስ ግን ከጥፋት የመጨረሻ ደረጃ ያዘውን ያለ ኃጢአቱ የስቅላት ሞት እየፈጸሙበት ያሉትን ሰዎች ምሕረት አድርጎላቸዋል። የእርሱን ፈለግ የተከተሉት እንደ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ የመሳሰሉትም ያደረጉት ይህንኑ ነው። በስሙ እስከተጠራን ድረስ ከእኛ የሚጠበቀውም ከዚህ ያላነሰ ነው።

እንደ ክርስቶስ ተከታይነታችን ከሆነ፤ ባንጠቃ የተሻለ ቢሆንም አጥቂ መሆኑ አይመረጥም። የአንጾኪያው ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ሐሳብ ሲያብራራ “በብዙ ሺህ ተኩላዎች የተከበብን በጎች ብንሆንም እረኛችን ኢየሱስ ያድነናል፤ ነገር ግን እኛ ራሳችን ተኩላ ከሆንን የሚደርስልን የለም” ይለናል።

ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን “መበቀል የእግዚአብሔር ፋንታ ነው፤ ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” ይለናል፤ የሰላም ንጉሥ ኢየሱስ በልባችን ነግሦ የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለማችን እንዲስፋፋ ያቅማችንን እንጣር።

የበደለኝን ይቅር ብዬ እንዳልፈው፤ ቂመኛ ልቤን ጌታ ሆይ ለውጠው!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት