እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ከቅዱስ ጳውሎስ ትምህርቶች በአጭሩ

ከቅዱስ ጳውሎስ ትምህርቶች አንዳንድ ነጥቦች በአጭሩ

መግቢያ

በሠላሳ ዓመት ወንጌላዊ አገልግሎቱ ትምህርቱንና ጥልቀቱን ለየት ያለ ስሜት ያሳደረበትን አንዳንድ ሐሳቦችን ብንጠቅስም እንኳ፤ መጨረሻው ይሄ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፤ ሆኖም ግን አንዳንዶቹን የጳውሎስን ታሪካዊ ሂደቶችና መሠረቶች ስንመለከት ግን ለትምህርቱና ሐሳቦቹን ምንጭ ሊሆን የሚችሉትን በመጠኑም ቢሆን መረዳት እንችላለን። ከነዚህ አንዳንዶቹን ለመግለጽ፦

  1. ጳውሎስ ከሞት የተነሣውን ክርስቶስ በራእይ ማየቱ፤
  2. የሁለተኛው መምጣት ግልጽ ያልሆነ ግንዛቤና ጥበቃ፤
  3. ግሪካውያን በቆሮንጦስ ትንሣኤ ሙታንን አለመቀበላቸው፤
  4. በኤፌሶን ያጋጠመው ለሞት የሚያደርስ አደጋ ጳውሎስ የክርስትናን ሕይወት ልክ እንደ ክርስቶስ ሥቃዮች እንዲመለከተው አስቻለው።
  5. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከሐሰት አስተማሪዎች ጋር መገናኘቱ - ይህ ግንኙነት የሐዋርያ እውነተኛ ማንነት ከመስቀል ጋር ያለውን ግንኙነት ተገነዘበ።
  6. ከአይሁድ እምነት ወደ ክርስትና የተለወጡ ክርስትያን በሙሴ ሕግና በክርስቲያናዊ ነጻነት በሚመለከት ያደረገው ክርክር፤ እምነትንና የጽድቅ ሥራን በሚመለከት የነበረውን ግንዛቤውን አዳበረለት።
  7. አይሁዳውያን ወንጌልን አንቀበልም አሉ፤ አረማውያን ግን ተቀበሉ።

በአዲስ ኪዳን የምናገኛቸው ጸሓፊዎች ካበረከቱት ጽሑፍ በስተጀርባ የሚገፋፋቸው ሌላ ዓይነት አስተሳሰብ አለ። ይህ አስተሳሰብ በተለይ ሕይወታቸውን፣ ጥሪያቸውን፣ ከክርስቶስ ጋር የነበራቸው የቅርብ ግንኙነት፣ ወይም ደግሞ ይሰብኳቸው ከነበሩ ማኅበረ-ምእመናን ግፊት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ሁሉ ስፋቱ፣ ጥልቀቱና ግልጽነቱ ተነሥተን የጳውሎስ መልእክቶች ዘርፈ ብዙነት ላይ የሚደርስ የለም ቢባል ማጋነን ሊሆን አይችልም።

ምስጢረ ፋሲካ፦ የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ብዙ ቅርንጫፍ እንዳለው እንደ አንድ ግንድ ሲታሰብ፤ ግንዱም ምስጢረ ፋሲካ ነው። ወይም ደግሞ ሌሎች ትምህርቶቹ እንደ ከዋክብት ስብስብ ቢቆጠሩ፤ ምሥጢረ ፋሲካ በመሃል ሆኖ እንደሚያበራ ፀሐይ ሊታሰብ ይችላል። ምሥጢረ ፋሲካ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረት ነው። የጳውሎስ ትምህርት፣ ሐሳቦችና ሕይወት በምሥጢረ ፋሲካ ዙርያ የሚሽከረከሩና የሚንቀሳቀሱ ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረው፣ ስለ ድኅነትና አፈጻጸሙ የሚናገረውና ስለ ልዕለ-ባሕርያዊ ወይም መንፈሳዊ ሰው የሚዘምረው፣ ሰለ ቤተክርስቲያን፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ዓለም መጨረሻ  ወዘተ . . .  የሚያቀርበው ትምህርት ዋና መሠረቱ የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ነው።

ጳውሎስ የሚናገረው ኃይለኛ ቃል አለ፤ “እኔ የተቀበልሁትን፤ በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፉላችሁ፤ ያስተላለፍሁላችሁም ነገር “በቅዱሳት መጻሕፍት ኣንደተጻፈው ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈውም በሦስተኛ ቀን ከሞት ተነሣ” የሚል ነው። ኣንዲሁም ለጴጥሮስ ታየ፤ ኋላም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ።” (1ቆሮ.15፤3-5)

ይህ ጥቅስ ጳውሎስ ከርሱ በፊት ከነበረው ትውፊት ጋር የነበረው ትስስር ግልጽ ምልክት ነው። ጳውሎስ የተቀበለውን ትምህርት በራሱ መንገድ በሰፊው አብራርቶ ለሌሎች ያስተላልፈዋል። “ሞቶ ተነሣ” የሚሉት ቃላት በጳውሎስ አባበል በአንድ ላይና በተደጋጋሚ የሚታዩ ናቸው። ለመጀመርያ ጊዜ ለማኅበረ-ክርስትያን የሚታውጀው የብሥራት ቃሎቹ የክርስቶስ ሞትና ትንሥኤ ናቸው (ሮሜ 8፤34፣ 14፤9፣ 2ቆሮ.5፤15፣ 1ተሰ.4፤14. . . ወዘተ)። ይህ ሁለቱ የመሞትና የመነሣት ክንዋኔዎች በመካከላቸው ያለው ግንኙነት የጊዜ ብቻ ሳይሆን (በተከታታይ መምጣታቸው)፤ የህላዌ ግንኙነትም ጭምር ነው። የተነሣው ክርስቶስ የተሰቀለውን የሚተካ ሳይሆን፤ የሞተው ራሱ “የክብር ጌታ”(1ቆሮ.2፤8) ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የከበረው ጌታ፤ ሥቃዮቹና ሞቱ በታማኝ ተከታዮቹ እየቀጠለ የሚኖር ነው። (2ቆሮ.4፤10)

 

የጳውሎስ መልእክቶች ዋና ዋና ትምህርቶች

  1. የክርስቶስ መስቀል፦ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ግዜ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር በተለይም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከመሞቱ ጕዳይ ሌላ ንም ነገር ላለማወቅ ወስኜ ነበር” (1ቆሮ.2፤2)። በጳውሎስ ግንዛቤ መስቀል የድኅነታችን፣ የነጻነታችን፣ የቤዛችን ምልክት ነው። ሰውን በባርነት ውስጥ አስገብቶት ከነበረው ኃጢአት ነጻ የሚያወጣ ነው። “አሁን ግን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበት መንገድ ከሕግ ነ?ፃ ሆኖ ተገልጦአል። ስለዚህ እግዚአብሔር ምንም ልዩነት ሳይስደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ጽድቅን ይሰጣል። ምክንያቱም ሰዎች ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋል፤ እግዚአብሒር የሰጣቸውንም ክብር አጥተዋል። ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው በአዳኝነት ሥራ፤ በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ይጸድቃሉ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋኦት አድርጎ ያቀርበው፤ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በደሙ የኃጢአታቸውን ያርታ እንዲያገኙ ነው፤ እግዚአብሒር ይህን ማድረጉ የቀድሞውን ኃጢአት እንዳልነበረ በመቍጠር የራሱን የጽድቅ መንገድ ለመግለጥ ነው። በአሁኑም ዘመን እግዚአብሔር ራሱ ጻድቅ ምሆኑን የሚያሳየው በኢየሱስ የሚይምኑትን ሁሉ በማጽደቅ ነው” (ሮሜ 3፤21-26)። “እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ብሎልናል . . . ይከሰንና ይቃወመን የነበረውን የዕዳ ጽሑፍ ደመሰሰ” (ቆላስ.2፤13-15) በዚህ ዓይነት “የእግዚአብሔር ጽድቅ” ይገለጻል (ሮሜ 3፤21-26)። ይህ ጽድቅ ከእግዚአብሔር ሕያውነትና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ጥሩ ፍላጎት የሚስማማ ነው። በሮሜ. 8፤31 “እግዚአብሔር ከኛ ጋር ስለኛ” ይላል።
  2. የእግዚአብሔር ጽድቅ፦ (Justification) እግዚአብሔር በክርስቶስ የፈጸመው፤ ሰው ባልጠበቀውና ባልገመተው መንገድ በኩል ስለኛ ያደረገው የድኅነት እቅድ የሚያረጋግጠው ነው አለ። ያገኘነው “ጽድቅ” ማለት “ከእግዚአብሔር ጋር ያደረግነውን ግንኙነት”፤ በችሎታችንና በድካማችን ከሚፈጸም ሥራዎቻችን ወይም ውጫዊ ሕግ በመፈጸም የተገኘ ሳይሆን፤ ባላደረግነው ወይም በነጻ ከተሰጠን፤ ነጻ ከሚያወጣው ከእግዚአብሔር ጸጋ ነው። “ሰዎች ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋል፤ እግዚአብሔር የሰጣቸውንም ክብር አጥተዋል። ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው በአዳኝነት ሥራ፤ በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ይጸድቃሉ።. . . ሰው የሕግን ሥራ በመፈጸሙ ሳይሆን በእምነት መሆኑን እንገነዘባለን።” (ሮሜ 3፤23-28) “እናንተ ሕግን በመፈጸም መጽደቅ የምትፈልጉ፤ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋውም ርቃችኋል። . . . እኔ የእግዚአብሔርን ጸጋ አልንቀውም። ምክንያቱም ጽድቅ ሕግን በመፈጸም የሚገኝ ከሆነ፤ ክርስቶስ የሞተው ለከንቱ ነው ማለት ነው።” (ሮሜ 5፤4፣ 2፤21)

ከላይ እንደተመልከትነው አሰቃቂ ከሆነው ከኢየሱስ ሞት ጋር ተያይዞ የምናገኘው፤ እርስ በራሱ የተሳሰረ ሐሳብና ቃላት አለ፤ ጸጋ - እምነት - ጽድቅ - ይህም ማለት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ኅብረትና አንድነት፤ በመጨረሻ ጊዜ የሚሰጥ ወይም እዛ የቆየን የሥራችን ውጤት ሳይሆን፤ በተቃራኒው እግዚአብሔር በክርስቶስ አድርጎ የሰጠን፤ በሚያስደንቅ ሁኔታ የሰጠን ነው (ሮሜ 5፤8)፣ ሰላም፣ ነጻነትና ደስታን በመስጠት ደግሞ ራሱን በሙላት የሚሰጥበት ሁኔታ ነው። (ሮሜ. 5፤1፣ 8፤1፣ ፊልጵ.1፤25 ተመልከት)

  1. አዲስ ሰው፦ በዚህ ዓይነት “አዲሱ ሰው” ሕይወት ያገኛል (ቆላ.3፤10፣ ኤፌ.4፤24)። ይህ የ“አዲስ ሰው” ሕይወት ወይም “አዲስ ፍጥረት” ደግም (ገላ.6፤15፣ 2ቆሮ.5፤17) እግዚአብሔር እግዚአብሔር ግርማ በሞላው ሕላዌው በዚህች ምድር እንደተገለጸ የሚያመለክት ነው። በዚህ ምክንያት በተለያየ ቦታ የሚገኙትን ማኅበረ ክርስትያን፤ ጳውሎስ “ቅዱሳን” እያለ ይጠራቸዋል (ሮሜ 1፤7፣ 1ቆሮ.1፤2፣ 2ቆሮ.1፤1፣ ኤፌ.1፤1፣ ፊልጵ.1፤1፣ ቆላስ.1፤2…)። ጳውሎስ “ቅዱሳን” ብሎ መጥራቱ ለወደፊቱ እንዲቀደሱ ባለው ፍላጎት፤ ወይም ደግሞ እንደ እቅድ ብቻ አስቦ ሳይሆን፤ በፊት የተቀበሉት ቅድስና እንዳለ ነው የሚታመነው። ስለዚህ ከክርስቶስ መስቀል በሕይወታችን ውስጥ ለሚያጋጥሙን የተለያዩ ስቃዮች ጠለቅ ያለ ትርጉም እናገኛለን። “የክርስቶስን መከራ በብዛት እንደመካፈላችን መጠን፤ እንዲሁም በክርስቶስ አማካይነት መጽናናትን በብዛት እናገኛለን።” (2ቆሮ.1፤5) እንዲሁም ክርስቶስንና የትንሣኤውን ሥልጣን ለማወቅ፤ ሥቃዩን መካፈል፣ በሞቱ እሱን እንድትመስለው፣ በትንሣኤ ሙታን ደግሞ ሱታፌ (አንድነት) ልታገኝ ትችላለህ (ፊልጵ.3፤10-11)። ይህ ሁሉ ግን “አካሉ ስለሆነችው ቤተክርስቲያን” (ቆላስ.1፤24)፤ “እጅግ ታላቅ የሆነ ዘላለማዊ ክብር” በመመልከት ነው (ሮሜ 9፤5፣ 2ቆሮ.4፤17)።
  2. ምሥጢረ ክርስቶስ፦ ስጢረ ፋሲካ በትንሣኤ ሙታንና በዘላለማዊ ሕይወት ዓይን ከተመለከትነው የሚሰጠው ፍሬዎች አሉት። “ክርስቶስ ከሞት ያልተነሣ ከሆነ፤ እምነታችሁ ከንቱ ነዋ። ገና በኃጢአታችሁ እንደጠፋችሁ ናችሁ ማለት ነው!” (1ቆሮ.15፤17)፤ አሁን ግን “እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። . . . ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ጌታ ነው ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ።” (ሮሜ.10፤9)፤ ስለዚህ “ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በአፍህ ብትመሰክርና እግዚአብሔር ከሞት እንዳነሣውም በልብህ ብታምን ትድናለህ” (ሮሜ 10፤9)። በዚህ ምክንያት ትንሣኤ ሙታን ትልቅ ትርጉም አለው። በትንሣኤው እሱ “በቅድስናው መንፈስ በኩል በታላቅ ኃይል ከሞት በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያበስር” ነው (ሮሜ 1፤4)። “በእግዚአብሔር ቀኝ” (ሮሜ 8፤34) ስለተቀመጠ ደግሞ፤ ሰብአዊ ሁኔታው ከምድራዊና ባሕርያዊ ወደ “መንፈሳዊና . . . ሰማያዊ” (1ቆሮ.15፤44.48) ተለወጠ። በዚህ ደግሞ ብዙ መዓረጎችን ተቀበለ፤ “ክርስቶስ” (ቅቡዕ)፣ “ጌታ” ወይም “እግዚአብሔር”፤ የ “ሰው ልጅ” የሚል መጠርያው በጳውሎስ መልእክቶች ላይ አይገኝም። “አዳኝ” የሚለው መጠርያው ደግሞ ዘግየት ብሎ ነው የሚመጣው። በጳውሎስ መልእክቶች ላይ ሌላ የምናገኘው የክርስቶስ መጠርያ “የመጨረሻው አዳም” (1ቆሮ.15፤22.45፣ ሮሜ 5፤12-21)፣ “ሕይወት የሚሰጥ” (1ቆሮ.15፤45) የቤተክርስቲያን “ራስ” (ቆላ.1፤18)፣ የአለቅነትና የሥልጣን “ራስ” (ቆላ.2፤10)፣ “የእግዚአብሔር መልክ” (2ቆሮ.4፤4፣ ቆላስ.1፤15)፣ “ለዘላለም የተባረከ እግዚአብሔር” (ሮሜ. 9፤5፣ ቆላ.2፤9)።
  3. መንፈስ ቅዱስ፦ ትንሣኤ ለክርስቶስ ብቻ አይደለም ከፍ ከፍ የሚያደርገው፤ የተነሣው ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አድርጎ በተከታዮቹ ላይ የሚያደርገው ሥራም የትንሥኤ ፍሬ ነው። ስለ “የልጁን መንፈስ” (ገላ.4፤6)፣ “የክርስቶስ መንፈስ” (ሮሜ 8፤9፣ ፊልጵ.1፤19) ጳውሎስ ለመጀመርያ ጊዜ የሚናገርበት ነው። እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ይህ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀታችን ጊዜ በልባችን የሠረፀ ሆኖ፤ ክርስቶስን እንድንመስል ወይም በክርስቶስ አምሳል እንደምንቀረጽ የሚያደርገን፤ የአዲሷ ሕይወት እርሾ በእኛ ላይ ነው። ይህ መንፈስ “ሥጋን” የሚቃወም፣ ከሥጋዊ ሕይወት አኗኗር ለየት ያለ ህላዌና ሕይወት የሚሰጥ ነው። (ሮሜ 8፤4-9) “በመንፈስ ብትመሩ ግን የሕግ ተገዥዎች አትሆኑም። . . . የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው” (ገላ.5፤18.22-23። “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ስለዚህ “አባባ” ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር የባርነትን መንፈስ  አልተቀበላችሁም” (ሮሜ 8፤14-15)።

ስለዚህ በክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም የጠበቀ ነው። እንደሱ ስለሆነ ደግሞ “በክርስቶስ ሕያው መሆን” ወይም ደግሞ “በመንፈስ ቅዱስ ሕያው መሆን” የሚል ወይም ደግሞ “በክርስቶስ መኖር” ወይም ደግሞ “በመንፈስ ቅዱስ መኖር” (ሮሜ 8፤1-2፣ 1ቆሮ.6፤11) የሚል አነጋገር በቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚገኝ ነው። በዚህ አባባሉ አድርጎ ጳውሎስ፤ የተጠመቀ ሰው “አዲስ ሕይወት” እንዴት መኖር እንዳለባት የሚያመለክት ነው። ይህ በቅድስት ሥላሴ ሕይወት ውስጥ ለመግባት በር የሚከፍትልን እንዲሆን “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፤ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችሁም ጋር ይሁን” (2ቆሮ.13፤13፣ ኤፌ.2፤18) በሚል ይገልጸዋል።

  1. ቤተ ክርስቲያን፦ ስለ ክርስቶስና ስለ መንፈስ ቅዱስ ከተባለው ነገር በመነሣት ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስትያን ያለው ግምትና ግንዛቤ  ልንመዝነው እንችላለን። “አይሁዳውያንም ብንሆን፤ ግሪካውያን ብንሆን፤ ባሪያዎችም ብንሆን፤ ነጻ ሰዎችም ብንሆን፤ አንድ አካል ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀናል፤ ሁላችንም ከዚሁ ከአንዱ መንፈስ ጠጥተናል” (1ቆሮ.12፤13) ይህ ለቤተክርስቲያን “የክርስቶስ ምሥጢራዊ አካል” የሚል አባባል የራሱ የጳውሎስ ነው። በ 1ቆሮ.12፤27፣ በሮሜ 12፤5 በግልጽ የሚነገርና የሚብራራ እንዲሆን፣ በሌላ ቦታ ደግሞ “ራስ” የሚለው ሐሳብ በቆላስ.1፤18፣ 2፤19 በኤፌ.1፤23፣ 4፤15 እናገኛለን። ይህ ሁሉ የጳውሎስ መልእክቶች ግልጽ ማድረግ የፈለጉት ነገር አለ፤ የቤተክርስትያን ማኅበራዊ መልክ ግልጽ ሲያደርግ ከክርስቶስ ጋር የሚኖረው አንድትና መዋሃድ ከሱ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። (ገላ.3፤28 “ሁላችሁም በክርስቶስ አንድ አካል ናችሁ”) እንደ “የእግዚአብሔር ሕዝብ” መጠን (1ቆሮ.10፤18፣ ገላ.6፤16፣ 3፤15-29)። “የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ” (1ቆሮ.3፤16-17፣ 2ቆሮ.6፤16፣ ኤፌ.2፤22)፣ የክርስቶስ “ሙሽራ” (ኤፌ.5፤22-32፣ 2ቆሮ.11፤2) ይህቺ ማኅበረ-ክርስቲያን “ኤክሌስያ” (አቅሌስያ/አቅላስያ) በውስጧ በብዙ አገልግሎቶች የቆመች ናት። እነዚህ አገልግሎቶች ደግሞ ሕይወት ከሚሰጣት መንፈስ ቅዱስ የሚመጣ መሆኑን ጳውሎስ ይታመናል። “ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉ። አንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ነው። . . . ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ኣንደ ፍሎጐቱ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታ ይሰጠዋል” (1ቆሮ.12፤4,11) ይህ የተለያየ ስጦታ ግን ለመለያየት መንገድ የሚከፍት አይደለም። ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ አንዲትና ሙሉ ሆና፤ የአንድነት ምልክት በሆነው መስቀል ስር ሆና፤ ከሱ በሚመነጨው ጥበብ (1ቆሮ.1፤1-4) ተመርታ የምትካሄድ ናት። የአስተዳደርም አገልግሎት ሳይቀር ከስጦታዎቹ ጋር ነው የሚቆጠረው (1ቆሮ.12፤28፣ ኤፌ.4፤11)። ሥራው ደግሞ ክርስቶስን መስበክ (1ቆሮ.9፤16-17፣ 2ቆሮ.4፤5) ማኅበራዊውን ሕይወት መጠበቅ (1ቆሮ.5፤1-5)፣ በማኅበራዊ ደስታ ጊዜ መሳተፍ (2ቆሮ.1፤23)
  2. ዳግመኛ መምጣትና የመጨረሻ ፍርድ፦ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ተስፋ የአንድ ክርስቲያን ውስጣዊ ኃይልና ሕይወት ነው። “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ቀን ያለነቀፋ ሆናችሁ እንድትገኙ፤ እርሱ እስከ መጨረሻ ጸንታችሁ እንድትኖሩ ያደርጋችኋል” (1ቆሮ.1፤8)። የተጠቀሰችው “ቀን” የትንሣኤ ቀን እንደምትሆን የግድ ነው። “እነሆ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ። ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። የምንለወጠውም የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ጊዜ ንደ ዓይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ። እኛም እንለወጣለን፤ምክንያቱም ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት።” (1ቆሮ.15፤51-53)

ከዚህ ጋር ወሳኝ የሆነ ፍርድ ይደረጋል። “እያንዳንዱ በሥጋው ላደረገው ክፉም ሆነ ደግ ነገር እንደየሥራው ብድራቱን ለመቀበል፤ ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት መቅረብ ነው” (2ቆሮ.5፤10)። ለጳውሎስ ዋና አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው “ከጌታ ጋር የምንኖር” መሆናችን ነው (1ተሰ.4፤17፣ ፊልጵ.1፤23፣ 3፤13.20-21፣ 1ቆሮ.1፤9)። “…በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ያማያውቁትንና ለጌታችን ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል። እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኃያሉ ክርቡ ተለይተው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ” (2ተሰ.1፤8-9)።

ስለዚህ ተስፋ ለሕይወት ዋና አስፈላጊና መሠረታዊ መመርያ ሆኖ ይገኛል። በዚህ መሠረት ደግሞ ለተጠመቀ ክርስትያን፤ ጳውሎስ የሚያስታውሰው ነገር አለ፦ “እኛ የምንመለከተው የማይታየውን እንጂ የሚታየውን አይደለም። ምክንያቱም የሚታየው ጊዜያዊ ነው፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው” (2ቆሮ.4፤18)። ምክንያቱም “በዓለም ሀብት የሚጠቀም፤ በሙሉ እንደማይጠቀም ሆኖ ይኑር። ምክንያቱም የአሁኑ ዓለም ሁኔታ አላፊ ነው” (1ቆሮ.7፤31)። የአንድ ክርስቲያን መዳን “አሁን” ነው የሚወሰነው ሊባል ይችላል። (2ቆሮ.6፤2) አሁኑኑ “በመስቀሉ ቃል” ፊት ተገኝተህ የሚድኑትና የሚጠፉት የትኞቹ እንደሆኑ ለመወሰን ብዙ አያስቸግርም (1ቆሮ.1፤18፣ 2ቆሮ.2፤15)። የአሁኑን ጊዜና የሚመጣውን ጊዜ በቀጣይነት የሚያገናኝ የሚያስተሳስር ደግሞ ፍቅር ነው። “እንግዲህ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ። ነገር ግን ከነዚህ መካከል ብልጫ ያለው ፍቅር ነው” (1ቆሮ.13፤13)።

በተረፈ “ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል የለም። ችግር ወም መከራ፤ ስደት ወይም ራብ፣ ራቁትነት ወይም አደጋ፣ ወይም ሰይፍ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን አይችልም። . .  . ሞትም ቢሆን፣ ህይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ባለሥልጣኖችም ቢሆኑ፣ የሰማይ ኃይሎችም ቢሆኑ፣ ከፍታም ኢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ማንኛውም ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከተገለጠልን ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ” (ሮሜ 8፤35.38-39)።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት