እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ጳውሎስና ሴቶች

ጳውሎስና ሴቶች

ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የሚናገር ወንድ ሁሉ፤ በወን ላይ ሥልጣን ያለውን ክርስቶስ ያዋርዳል። እንዲሁም ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የምትናገር ሴት፤ በሴት ላይ ሥልጣን ያለውን ወንድ ታዋርዳለች። ምክንያቱም ራስዋን የማትከናነብ ሴት እንደተላጨች ትቈጠራለች” (1ቆሮ.11፤4-5)

ወንድና ሴት በእግዚአብሔር ፊት ያላቸው እኩልነት ለጳውሎስ ግልጽ ነው። ቢሆንም ግን በቤተክርስቲያንና በኅብረተሰብ መካከላ ያላቸው የጥሪና የአገልግሎት ልዩነት በዚህ የእኩልነት አቋም ይወገዳል ማለት አይደለም።

ቅዱስ ጳውሎስ የሴት ጠላት እንደነበር ወይም ደግሞ ሴትን የሚያዋርድ (የሚንቅ) እንደነበር ማረጋገጫ ይገኛልን? እሱ ራሱ ከትዳር ይልቅ ሳያገባ መኖርን መምረጡ ከክርስትና ሕይወት ጋር የሚሄድ ነው። ለቆሮንቶስ ሰዎች ልክ የእሱን ዓይነት ሕይወት እንዲይዙ ማለትም ሳያገቡ እንዲኖሩ መምከሩ፤ በቆሮንጦስ የነበረውን ልቅ ዓይነት ሕይወትን ተመልክቶ ያስተላለፈው በመሆኑ የሚያስደንቅ ምክር አይደለም። የቆሮንጦስ ሰዎች በሜዲትራንያን አካባቢ ቅጥ በሌለው በምንዝርና ሕይወታቸው የታወቁ ነበሩ። ቢሆንም ግን “… ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር የተለየ ስጦታ ሰጥቶታል፤ አንዱ አንድ ዓይነት ስጦታ፤ ሌላውም ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው” (1ቆሮ.7፤7)

ብዙ የቅዱስ ጳውሎስን ጽሑፍ የሚያነቡ፣ አንብበውም የሚመራመሩ፣ ዛሬም ያሉ በፊትም የነበሩ፤ ጳውሎስ ስለ ሴት የነበረውን አስተሳሰብ ግልጽ ሊያደርጉ ይፈልጋሉ። ሆኖም ግን በመጨረሻ ላይ የሚሰጡት ድምዳሜ እንደብዛታቸው የተለያየ ነው።

በተለይ ደግሞ ክርስቲያን ሴት  ልጅ ቅዱስ ጳውሎስ የሚለውን አንዱን ክፍል ብቻ ይዛ፤ ጥያቄ ልትጠይቅ፣ እውነተኛ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ለማወቅ እንደምትጠይቅ ጥርጥር የለውም።

ጳውሎስ የጠርሴስ ልጅ እንደመሆኑ መጠን፤ በጥንታዊት ቤተክርስቲያን ልዩ ቦታ የነበረውና ልዩ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው ነው። የእርሱ መልእክቶች ወንጌል ከመጻፉ በፊት የተጻፉና የተሰራጩ በመሆናቸው በመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖቹ ሕይወት ላይ የተወው ጫና በጣም ግልጽ ነው። ስለ ጳውሎስ የሕይወት ታሪክና ማንነትና ሐሳቦች ምንጮቻችን የሐዋርያት ሥራና የራሱ መልእክቶች ናቸው።

አስተዳደጉና የተኮተኮተበትን ሁኔታም ከተመለከትን እሱ በጣም ሕግ አጥባቂዎች ከሆኑት ከአይሁድ ወገን ሲሆን (የሐዋ.22፤3፣ ፊልጵ. 3፤5-6)፤  በደማስቆ መንገድ ላይ የተፈጸመው ፍጻሜ፣ ጳውሎስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መመለሱና መለወጡ፣ የነበረውን አስተሳሰብ፣ አኗኗርና አመለካከት ገለባበጠበት። በፊት ከነበረው ሐሳቦች የተለየ መንገድ እንደሚይዝ አደረገው። ከአረማዊነት ሆነ ከአይሁድነት ወደ ክርስትና የመጡትን ማኅበራተ-ክርስትና በመሠረተበትም ጊዜም ቢሆን ግላዊ አስተሳሰቡን፣ ካገኛቸው ኅብረተሰብ አኗኗር፣ በግልጽ ከክርስትና ሕይወትና ከወንጌል ትምህርት፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ከመጣው ትምህርት ጋር የማይቃረነውን ሁሉ ተጠቀመበት። ሴቶችን በሚመለከት የነበረው አስተሳሰብ ደግሞ ከአባባሉና አጻጻፉ የምንገነዘበው ነው። ብቁዎችና ጎበዝ የስብከተ ወንጌል ተባባሪ የሆኑ ሴቶች እንደነበሩት ጳውሎስ ራሱ የሚገልጸው ነው። ፌቨንን ብቻ መጥቀስ ይበቃል። በቅንክርኤ ቤተክርስቲያን ዲያቆን የነበረች ናት (ሮሜ.16፤1)። ፌቨን ብቻ ሳትሆን በእምነት ብሩህ ኮከቦች የነበሩትን የጢሞቴዎስ እናትንና አያትን፤ ሌሎችም ቤተክርስቲያንን እምነት በማነጽ እንደ ምሳሌ የጠቅሳቸዋል። በገላትያ መልእክት ውስጥ በእምነቷ ሣራ ብቻ ሳይሆን፤ ማርያምንም አዳኙን በሥጋ በመውለዷ ይጠቅሳታል (ገላ.4፤5፣ 4፤21)።

በኦሪት ዘፍጥረት የመጀመርያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ስለ ሰው አፈጣጠር የሚናገሩ አሉ። “አምላክ ሰውን ፈጠረ፤ . . . ወንድና ሴትም አድርጎ ፈጠራቸው” (1፤27) “እግዚአብሔር አምላክ አፈር ከመሬት ወስዶ ሰውን ፈጠረው፤ . .. “ከአዳም ከወሰዳት አጥንት ደግሞ ሴትን ፈጠረ” (2፤7.22) ” በምዕራፍ ሦስት አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንዳፈረሱ ይናገራል። “ሔዋን ደግሞ . .  ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች፤ ለአዳምም ሰጠችው፤ እሱም በላ”። (3፤6)።

ስለዚህ በ54-56 አካባቢ ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈው የመጀመርያው ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች “ባል የሚስት ራስ ነው” ሲል ሳለ፤ ለዚህ ደግሞ እንደ መከላከያ አድርጎ “ሴት ከወንድ እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም” ሲል (1ቆሮ.11፤3,8) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 22 ያለውን በማሰብ እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም። ከሱም ጋር ጥንታዊ ልማድና የአይሁድ አስተሳሰብ፤ ለሴቶች ምንም ግምት የማይሰጥ በጳውሎስ ጭንቅላት ውስጥ እንዳለ መዘንጋት የለብንም።

በዚህ ሁሉ አስተሳሰብና ልማድና ሁኔታ ያደገ ጳውሎስ፤ እዚህ ላይ የሰጠውን ድምዳሜውን በመድረሱ፤ ማለት ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት መንፈሳዊ ጉባኤ ሴቶች እንዲናገሩ አለመፍቀዱ የሚያስገርም አይደለም። በጊዜው ልማድ ለመናገር የሚያበቃ እውቀትና ትምህርት እንዳልነበራቸው ግልጽ ነው። (1ቆሮ.11፤3-13፤ 14፤34-35)

ተመሳሳይ ሐሳቦች በሌሎቹ ጽሑፎቹ የማይገኝ አይደለም (ኤፌ.5፤22-23፣ 1ጢሞ.2፤9-15)። ከአረማዊነት ወደ ክርስትና የገቡ የገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክት፤ የጳውሎስ ትምህርተ-መለኮታዊ አትኩሮት የሚገልጹ ብሩሕ ቃላቶች እናገኛለን። “ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ስለሆናችሁ በአይሁዳዊና በግሪካዊ፣ በአገልጋይና በጌታ፣ በወንድና በሴት መካከል ምንም ልዩነት የለም” (ገላ.3፤28)። “ወንድ ሴት” የሚለው አባባል በኦሪት ዘፍጥረት 1፤27 ያለውን እንደሚያመለክት ጥርጥር የለውም። በተለይ በግሪካዊ አባባሉ ድሮ በሰባ ሊቃውንት (ሴፕትዋጂንት) ያለውን የሚያንጸባርቅ ነው።

በጊዜያችን ቤተክርስቲያን በጉባኤዎች አድርጋ የምታስተምረው ትምህርት፤ በተለይ ስለ ግልጸት ወይም የአምላክ ቃል በሚናገረው ቁጥር 12 ላይ የሚሠጠው መሠረታዊ ነጥብ አለ “እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ በሰዎችና በሰዎች አደራረግ አድርጎ ስለሚናገረን፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጓሜ የሚተነትን ሰው፣ ልክ አምላክ ሊገልጽልን በፈለገው ዓይነት እንዲገባው ከፈለገ፤ ጸሐፊዎቹ ሊሉትና ሊረዱት የፈለጉትን ትርጓሜ፤ እንዲሁም አምላክ በቃላቶቻቸው አድርቶ ሊገልጸው የፈለገውን ሁሉ ለማወቅ በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልገዋል።” የአምላክ ቃል የጊዜውን አነጋገርና አቀራረብ ወስዶ ነው ወደኛ የሚመጣው። እኛ ግን ከጊዜ ጋር የሚለዋወጠውንና የማይለዋወጠን ለይተን ለማየት እንጥራለን። ሥነ ሥርዓትን በሚመለከትና እምነትንና ድኅነትን በሚመለከት ለይተን መመልከት ይኖርብናል። ስለ ሴቶች የሚሰጠው መመርያ ደግሞ የሥነ ሥርዓት ጉዳይ ልማድ እንጂ እንደ ትምህተ መለኮት፤ ወይም ደግሞ ያለ እኩልነት ምልክት ሆኖ መወሰድ የለበትም።

ይህ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ስለ ሴቶች የተናገረውን ግልጽ ሊያደርግልን ይችላል። ስለዚህ ጳውሎስ የሚለውን ሁሉ ከጊዜው ሁኔታ ጋር አዛምደን ካነበብነው፤ ጳውሎስ የሴቶች ተቃዋሚ ሳይሆን ደጋፊ እንደሆነ ነው የሚረዳን። ባለፉት ዘመናት ቅዱስ ጳውሎስን በሚመለከት ብዙ ጽሑፎችን ያበረከቱ ስለ ሴቶች ያለውን አቋም ሲያንጸባርቁ የነበራቸው የግንዛቤ ችግር ቃላቱን ከነባራዊው ሁኔታ ነጥለው መውሰዳቸው ነው። ከአባባሉ በስተጀርባ ያለውን፤ ወይም በመሥመሮች መካከል የተጻፈውን ድባብ ቆፍረን ማግኘቱ ትክክለኛውን ሁኔታ መገንዘብ ያስችለናል።


የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት