መደምደምያ
- Category: የዮሐንስ ወንጌል 6፡1-15 ጥናት
- Published: Friday, 29 July 2011 11:42
- Written by Super User
- Hits: 3768
- 29 Jul
መደምደምያ
በጥናታችን ፡ መነሻ ፡ ላይ ፡ አምስት ፡ እንጀራ ፡ እና ፡ ሁለት ፡ ዓሣ ፡ አባዝቶ ፡ ቁጥራቸው ፡ ከአምስት ፡ ሺህ ፡ በላይ ፡ ለሆኑ ፡ ሰዎች ፡ መግቦ ፡ አሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ያህል ፡ ቁርስራሽ ፡ መሰብሰብ ፡ እንደ ፡ ታምራት ፡ ወይስ ፡ አንደ ፡ አስማት ፡ ይቆጠራል ፡ የሚለውን ፡ ሀሳብ ፡ አንስተን ፡ ነበር ፡፡ በጥናታችንም ፡ ሂደት ፡ ላይ ፡ ታሪኩን ፡ በተለያየ ፡ መልኩ ፡ ለማብራራትና ፡ ለመረዳትም ፡ ሞክረናል ፡፡ አብዛኞቻችን ፡ በጥናቱ ፡ ውስጥ ፡ ለጥያቄው ፡ መልስ ፡ የሚሆነን ፡ ማብራሪያ ፡ አግኝተን ፡ ይሆናል ፡፡ በተለይም ፡ ከምሥጢረ ፡ ቅ.ቁርባን ፡ ጋር ፡ በተያያዘ ፡ መልኩ ፡ በተደረገው ፡ ገለጻ ፡ ታሪኩን ፡ የበለጠ ፡ ለመረዳት ፡ ይጠቅማል ፡ ብለን ፡ እናምናለን ፡፡
አሁንም ፡ አስቲ ፡ ጌ.ኢ.ክ ፡ ይህንን ፡ ታምራት ፡ አላከናወነም ፤ ይህ ፡ ታሪክ ፡ ሌላ ፡ ተጨማሪ ፡ የሆነ ፡ የተሸሸገ ፡ መልእክት ፡ አለው ፡ እንጂ ፡ እንዲያው ፡ እንጀራና ፡ ዳቦ ፡ አባዝቶ ፡ አብልቶና ፡ አጥግቦ ፡ አሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ቁርስራሽ ፡ ሰበሰበ ፡ ብንል ፡ አስማተኝነትን ፡ ያሳያል ፡ እንጂ ፡ ታምራትን ፡ አያሳይም ፡ የሚሉትን ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ሊቃውንቶች ፡ ሀሳብ ፡ እናክልበት ፡፡ እንደነዚህ ፡ ሊቃውንቶች ፡ አገላለጽ ፡ በወቅቱ ፡ ኢየሱስ ፡ ያስተምረው ፡ የነበረው ፡ ሕዝብ ፡ በጣም ፡ ራስ ፡ ወዳድ ፡ የሆነ ፣ ለራሱ ፡ ብቻ ፡ የሚኖር ፣ ተከፋፍሎ ፡ መብላትን ፡ የማያውቅና ፡ የወንድማማችነትን ፡ ፍቅር ፡ የራቀው ፡ ሀይለኛ ፡ የሆነ ፡ ማህበረሰብ ፡ እንደነበር ፡ ይገልጻሉ ፡፡ ይህ ፡ ሕዝብ ፡ ታድያ ፡ ወደ ፡ አንድ ፡ የስብሰባ ፡ ቦታ ፡ ወይም ፡ ከአካባቢው ፡ ራቅ ፡ ብሎ ፡ ሲሄድ ፡ የየራሱ ፡ የሆነ ፡ የሚበላ ፡ ነገር ፡ ይዞ ፡ ይንቀሳቀስ ፡ ነበር ፡፡ የያዘውንም ፡ ምግብ ፡ ይሞታታል ፡ እንጂ ፡ በምንም ፡ ይሁን ፡ በምንም ፡ ጉዳይ ፡ ከሌላው ፡ ጋር ፡ ተከፋፍሎ ፡ አይበላውም ፡ ነበር ፡፡ የኢየሱስንም ፡ ትምህርት ፡ ለመከታተል ፡ ቀዬአቸውን ፡ ጥለው ፡ ራቅ ወዳለው ፡ ተራራ ፡ ለረጅም ፡ ሰዓት ፡ ከሱ ፡ ጋር ፡ ወይም ፡ እሱን ፡ እያደመጡት ፡ ለመቆየት ፡ ሲሄዱም ፡ እያንዳንዱ ፡ የራሱ ፡ የሆነ ፡ ምግብ ፡ ይዞ ፡ ነበር ፡ የሚሄደው ፡፡ እነዚህ ፡ ሕዝቦች ፡ ታድያ ፡ ለረዥም ፡ ሰዓታት ፡ ኢየሱስን ፡ ሲያደምጡ ፡ ቆይተዋል ፤ ስለምን ፡ ግን ፡ እንዳስተማራቸው ፡ በወንጌሉ ፡ አልተገለጸም ፡፡ በእርግጥ ፡ በአዲስ ፡ ኪዳን ፡ ውስጥ ፡ ያለው ፡ ጌ.ኢ.ክ. ያስተማረው ፡ ትምህርት ፡ በሙሉ ፡ ባጭሩ ፡ ቢገለጽ ፡ ሁለት ፡ ነገሮች ፡ ብቻ ፡ ናቸው ፡፡ እነዚህም ፡ የእግዚአብሔር ፡ ፍቅርና ፡ የባልንጀራ ፡ ፍቅር ፡ ናቸው ፡፡ እነዚህ ፡ በምንም ፡ መልኩ ፡ የማይለያዩ ፡ የ.ጌ.ኢ.ክ ፡ ትምህርቶች ፡ ፍቅር ፡ ወደ ፡ ላይ ፡ እና ፡ ፍቅር ፡ ወደ ፡ ጎን ፡ በመባልም ፡ በጌ.ኢ.ክ ፡ መስቀልም ፡ ይመሰላሉ ፡፡ ይህም ፡ ጌ.ኢ.ክ. እጆቹን ፡ ወደ ፡ ጎን ፡ ተደርጎ ፡ መስቀል ፡ ላይ ፡ መቸንከሩን ፡ በባልንጀራ ፡ ፈቅር ፡ ሲገለጽ ፡ እራሱንና ፡ እገሮቹን ፡ ወደ ፡ ላይና ፡ ወደ ፡ ታች ፡ መሆናቸው ፡ ደግሞ ፡ የእግዚአበሔር ፡ ፍቅር ፡ መግለጹን ፡ ነው ፡፡ ከዚህም ፡ በተጨማሪ ፡ አንድምታ ፡ ዮሐ 14 ፡ 21 ፡ አምስቱ ፡ እንጀራና ፡ ሁለቱን ፡ ዓሣ ፡ እንዲህ ፡ በማለት ፡ ይፈታዋል ፤ « አምስቱ ፡ ያምስቱ ፡ አዕማደ ፡ ምሥጢር ፤ ሁለቱ ፡ ዓሣ ፡ የፍቅረ ፡ ቢጽና (የባልንጀራ) ፡ የፍቅረ ፡ እግዚአብሔር ›› ምልክት ፡ እንደሆን ፡ ይተነትነዋል ፡፡
ስለዚህ ፡ እነዚህ ፡ ሕዝቦች ፡ ተራራው ፡ ላይ ፡ ከኢየሱስ ፡ ሲያደምጡት ፡ የዋሉት ፡ ስለ ፡ እግዚአብሔር ፡ ፍቅርና ፡ ስለ ፡ ወንድማማችነት ፡ ፍቅር ፡ ነበር ፡ ማለት ፡ ነው ፡፡ ታድያ ፡ በትምህርቱ ፡ ልባቸው ፡ በጣም ፡ ስለተነካ ፡ ወድያውኑ ፡ የለውጥ ፡ ሂደት ፡ ጀመሩ ፡፡ በትምህርቱም ፡ መጨረሻ ፡ ላይ ፡ ሕዝቡ ፡ በረሃብ ፡ ስለተንገላታ ፡ ምግብ ፡ አስፈለገ ፡፡ ከሕዝቡ ፡ መካከል ፡ ደግሞ ፡ በኢየሱስ ፡ ትምህርት ፡ ልቡ ፡ እጅግ ፡ በጣም ፡ የተነካው ፡ ፈጠን ፡ በማለት ፡ እኔ ፡ ዘንድ ፡ አምስት ፡ እንጀራና ፡ ሁለት ፡ ዓሣዎች ፡ አሉ ፡ በማለት ፡ ለጋራ ፡ አገልግሎት ፡ ሲያበረክት ፡ ሌላውም ፡ ሕዝብ ፡ ራስ ፡ ወዳድነቱን ፡ አሸንፎ ፡ የወንድማማችነትን ፡ ፍቅር ፡ ተላብሶ ፡ ያለውን ፡ በሙሉ ፡ በኢየሱስ ፡ እግር ፡ ሥር ፡ ማኖር ፡ ጀመረ ፡፡ ያኔ ፡ የፍቅር ፡ ሥራ ፡ በሕዝቡ ፡ ዘንድ ፡ ተከናወነ ፡፡ ኢየሱስም ፡ ያንን ፡ ባርኮ ፡ አከፋፈላቸው ፡፡ በዚህ ፡ መልኩ ፡ በፍቅር ፡ ተገፋፍተው ፡ የፍቅርን ፡ ሥራ ፡ ሰርተው ፡ በወንድማማችነት ፡ መንፈስ ፡ በአንድ ፡ ማዕድ ፡ ዙርያ ፡ ተሰባስበው ፡ ያቀረቡትን ፡ ሁሉ ፡ በኢየሱስ ፡ ተባርኮላቸው ፡ ስለበሉ ፡ ከታሰበው ፡ በላይ ፡ የተትረፈረፈ ፡ ምግብ ፡ ሊሰበሰብ ፡ ቻለ ፡ በማለት ፡ ያብራሩታል ፡፡
የእነዚህ ፡ ሊቃውንት ፡ ማብራርያ ፡ ትምህርት ፡ ሰጪነቱና ፡ የታምራቱን ፡ ትርጓሜ ፡ የበለጠ ፡ ለመረዳት ፡ የግንዛቤ ፡ አድማስ ፡ ማስፋቱ ፡ ምንም ፡ አይነት ፡ ጥርጣሬ ፡ የለውም ፡፡ በተለይም ፡ ነገሩን ፡ ከፍቅር ፡ ሥራ ፡ ጋር ፡ በማያያዝ ፡ ማለትም ፡ የኢየሱስን ፡ ቃል ፡ በደንብ ፡ የተረዳ ፡ ሰው ፡ ከእኔነቱ ፡ ወይም ፡ ከራስ ፡ ወዳድነቱን ፡ ወጥቶ ፡ ለሌሎች ፡ በማሰብ ፡ ያለውን ፡ ፍቅርም ፡ ሆነ ፡ ንብረት ፡ ከሌሎች ፡ ጋር ፡ በበጎ ፡ ፈቃደኝነት ፡ ወደ ፡ ማከፋፈል ፡ ውሳኔ ፡ መድረሱ ፡ አንድ ፡ የለውጥ ፡ ሂደት ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን ፡ የኢየሱስ ፡ ቃል ፡ በጎ ፡ ፈቃድ ፡ ባላቸው ፡ ሰዎች ፡ ሕይወት ፡ ውስጥ ፡ ገብቶ ፡ ወድያውኑ ፡ ፍሬ ፡ እንደሚያፈራ ፡ የሚያሳይ ፡ ነው ፡፡ ነገር ፡ ግን ፡ ከላይ ፡ ካየናቸው ፡ ማብራሪያዎች ፡ ሁሉ ፡ የትኛው ፡ የተሻለ ፡ ነው ፡ ወይም ፡ የበለጠ ፡ ትርጉም ፡ ያለው ፡ የትኛው ፡ ነው ፡ ወይም ፡ ትክክለኛ ፡ ትርጉሙ ፡ ይህ ፡ ነው ፡ በማለት ፡ መወሰን ፡ ስለማይቻል ፡ እያንዳንዱ ፡ አንባቢ ፡ ለራሱ ፡ መንፈሳዊ ፡ ሕይወት ፡ የበለጠ ፡ ትርጉም ፡ የሚሰጥለትን ፡ የመምረጥ ፡ ባለ ፡ ሙሉ ፡ መብትነቱ ፡ የተረጋገጠ ፡ ነው ፡፡ በእኛ ፡ እይታ ፡ ግን ፡ ዮሐ 6 ፡ እንዳለ ፡ በማንበብ ፡ ከምሥጢረ ፡ ቅ.ቁርባን ፡ ጋር ፡ ያለው ፡ ግኑኝነት ፡ በትኩረት ፡ እንዲታይና ፡ እንድናስተነትንበት ፡ ግብዣችን ፡ ነው ፡፡
ይህንን ፡ ትምህርታችን ፡ የምናጠቃልለው ፡ በዮሐ 6 ፡ 15 ፡ ላይ ፡ በተገለጸው ፡ የምስክርነት ፡ ቃል ፡ ይሆናል ፡፡ ሦስቱም ፡ ወንጌላውያን (ማቴ ፣ ማር እና ሉቃ) ፡ ይህንን ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ የሚደመድሙት ፡ ሕዝቡ ፡ በሙሉ ፡ በልተው ፡ እንደጠገቡና ፡ አሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ቀሪ ፡ ምግብ ፡ እንደተሰበሰበ ፡ በመግለጽ ፡ ብቻ ፡ ሲሆን ፡ ቅ.ዮሐንስ ፡ ግን « ሰዎቹም ፡ ኢየሱስ ፡ ያደረገውን ፡ ታምራዊ ፡ ምልክት ፡ ካዩ ፡ በኃላ ፡ ወደ ፡ ዓለም ፡ የሚመጣው ፡ ነብይ ፡ በእርግጥ ፡ ይህ ፡ ነው ›› ብለው ፡ ሲመሰክሩና ፡ ሊያነግሱትም ፡ ፈልገው ፡ እንደነበር ፡ የገልጻል ፡፡ ኢየሱስም ፡ ይህንን ፡ ሀሳባቸውን ፡ ዐውቆ ፡ እንደ ፡ ገና ፡ ብቻውን ፡ ወደ ፡ ተራራ ፡ ገለል ፡ እንዳለ ፡ ቅ. ዮሐንስ ፡ አበክሮ ፡ ይገልጻል ፡፡ በእርግጥም ፡ ቅ.ዮሐንስ ፡ በወንጌሉ ፡ ውስጥ ፡ በተለያየ ፡ ቦታዎች ፡ የምስክርነትን ፡ አስፈላጊነት ፡ አበክሮ ፡ ይገልጻል ፡፡ እንደ ፡ ቅ.ዮሐንስ ፡ አመለካከት ፡ ኢየሱስን ፡ ያገኘ ፣ ከኢየሱስ ፡ የተወሰነ ፡ ጊዜ ፡ እንኳን ፡ የሳለፈ ፣ በኢየሱስ ፡ የተፈወሰ ፣ በኢየሱስ ፡ ከጨለማ ፡ ወደ ፡ ብርሃን ፡ የተሸጋገረ ፣ በአጠቃላይ ፡ በኢየሱስ ፡ ሕይወቱን ፡ የተቀየረ ፡ ዝም ፡ አይልም ፤ ማለትም ፡ አይችልም ፤ ፍቅሩ ፡ ግድ ፡ ይለዋልና ፡ ፍርሃትንና ፡ ይሉኝታን ፡ አውልቆ ፡ በመጣል ፡ ያመሰግናል ፣ ይመሰክራል ፣ የተደረገለትንም ፡ ይተርካል ፣ ለሌሎችም ፡ አንተም ፡ ናና ፡ እይ ፡ በማለት ፡ መንገዱን ፡ ያሳያል ፡፡ ለምሳሌ ፡ ፊልጶስ ፡ ኢየሱስን ፡ ካገኘው ፡ በኋላ ፡ ለናትናኤል « መጥተህ ፡ እይ ›› አለው ፡፡ ሳምራዊቷም « እንስራዋን ፡ ትታ ፡ ወደ ፡ ከተማ ፡ ተመለሰች ፤ ለሕዝቡም ፡ ያደረግሁትን ፡ ሁሉ ፡ የነገረኝን ፡ ኑና ፡ እዩ ፤ እርሱ ፡ ክርስቶስ ፡ ይሆን ፡ እንዴ ?›› እያለች ፡ መሰከረች (ዮሐ 4 ፡ 28) ፡፡ ዐይነ ፡ ስውር ፡ ሆኖ ፡ የተወለደውን ፡ ሰው ፡ በኢየሱስ ፡ ከተፈወሰ ፡ በኋላ ፡ ፈሪሳውያን ፡ ይዘውት « ዐይንህን ፡ ስለ ፡ ከፈተው ፡ ሰው ፡ እንግዲህ ፡ አንተ ፡ ምን ፡ ትላለህ ?›› ሲሉት ፡ በድፍረት ፡ አጥማጆቹን ፡ ፈሪሳውያንን ፡ ቅንጣት ፡ እንኳ ፡ ሳይፈራ « እርሱ ፡ ነብይ ፡ ነው ፡ እናንተም ፡ ደቀ ፡ መዛሙርቱ ፡ ልትሆኑ ፡ ተሻላችሁ ? ›› በማለት ፡ ነው ፡ ምስክርነቱን ፡ በመግለጽ ፡ ያፋጠጣቸው (ዮሐ 9 ፡ 26-28) ፡፡ ስለዚህ ፡ ቅ.ዮሐንስ ፡ ለእያንዳንዳችን ፡ በእለታዊ ፡ ሕይወታችን ፡ ውስጥ ፡ ስለ ፡ እምነታችንና ፡ ስላመነው ፡ ማንነት ፡ በየትኛውም ፡ ቦታም ፡ ሆነ ፡ በየትኛውም ፡ ሁኔታ ፡ ውስጥ ፡ ምንም ፡ ሳንፈራና ፡ ሳናፍር ፡ እንድንመሰክር ፡ ጥሪውን ፡ ያስተላልፍልናል ፡፡
አይሁዳውያን ፡ ኢየሱስን ፡ ሊያነግሡት ፡ የፈለጉት ፡ በእርግጥ ፡ በልተው ፡ ስለጠገቡና ፡ ሌሎችም ፡ ታምራቶች ፡ ስላዩ ፡ ነው ፡፡ አንድምታ ዮሐ 6 ፡ 15 ፡ እንደሚለው « ቢራቡ ፡ ያመሳል ፣ ቢታመሙ ፡ ይፈውሳል ፣ ቢሞቱ ፡ ያስነሣልና ፡ እንዲህ ፡ ያለውን ፡ ቢያነግሡት ፡ እንደወደዱ ፡ አውቆባቸው ፡ ለብቻው ፡ ወደ ፡ ተራራ ፡ ሄደ ›› ይላል ፡፡ ስለዚህ ፡ የምናመሰግነው ፡ ወይም ፡ የምንመሰክረው ፡ አንድ ፡ ጥቅም ፡ ስላገኘን ፡ ወይም ፡ ስለተደረገልን ፡ ነገር ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን ፡ የሕይወታችን ፡ ሁሉ ፡ መሠረት ፡ ከመሆኑም ፡ አልፎ ፡ ያለ ፡ እርሱ ፡ መኖር ፡ የማንችል ፡ ወይም ፡ እኛነታችን ፡ ሁሉ ፡ የታነጸው ፡ በእርሱ ፡ መሆኑን ፡ አውቀን « ቢመችም ፡ ባይመችም ›› እንደሚለው ፡ ሐ. ጳውሎስ ፡ ሁሌም ፡ ለማመስገንና ፡ ለመመስከር ፡ ታጥቀን ፡ ዝግጁዎች ፡ በመሆን ፡ እንቁም ፡፡ ለዚሁም ፡ እግዚአብሔር ፡ እራሱ ፡ ይርዳን ፡ አሜን ፡፡
ከአባ ፡ ምሥራቅ ፡ ጥዩ