እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፮ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ሆሴዕ)

ክፍል ሦስት (ትምህርት ሃያ ስድስት)

የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - ትንቢተ ሆሴዕ

 

  • ነቢዩ ሆሴዕ የሚለው ስም ትርጓሜው ምን ያመለክታል? የነቢዩ ሆሴዕ ቤተሰባዊ ሕይወትና የነቢይነት አገልግሎት ጅማሬው ምን ይመስላል?

Hoseaትንቢተ ሆሴዕ ታናናሽ ነቢያት ተብለው ከተመደቡት ዐሥራ ሁለቱ ነቢያት ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ሆሴዕየሚለውስምሆሻ-ያ”ከሚለውስምጋርተዛማጅነት ያለውሲሆንትርጓሜውም “እግዚአብሔር ረድቷል” ማለት ነው፡፡  “ሆሻያ” የሚለው ስም በተቀራራቢነት ኢየሱስ እና ኢያሱ ከሚሉት ስሞች ጋር ስለሚዛመድ “እግዚአብሔር ያድናል” በሚለውም ጭምር ይተረጐማል፡፡ ሆሴዕየብኤርልጅእንደሆነተገልጿል (ሆሴ1)፡፡ነብዩሆሴዕሰማርያበሰባትመቶሃያአንድዓመተዓለም ተሸንፋ ከመፍረስዋበፊት የእስራኤል የፖለቲካ ሕይወት ባልተረጋጋበትና እጅግ በጣም አስቸጋሪ በነበረበት ጊዜበተለይም ከ755 እስከ 725 ዓ.ዓ ገደማ በእስራኤል ግዛት ወይም በሰሜናዊው መንግሥት ውስጥ የትንቢትቃልያስተላለፈነቢይነው፡፡ ይህ ወቅት በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባር ብልሹነት፣ ኢፍትሐዊ የሆነ የአስተዳደር ሕይወት የሰፈነበት፣ የድኾችን መብት የተረገጠበት በአጠቃላይ የሕዝቡ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ አኗኗር የተናጋበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ፈታኝ በሆነና የኑሮ ብልሹነት በተንሰራፋበት ወቅት ነው የነቢይነት መልእክቱን ለሰሜኑ ግዛት (ለእስራኤል ሕዝብ) ያስተላለፈው፡፡

መጽሐፉ ካካተታቸው የተወሰኑ መረጃዎች በመነሣት ስለ ነቢዩ ሆሴዕ ቤተሰባዊ ሕይወት በተወሰነ መልኩ ቢሆንም መናገር ይቻላል፡፡ ሆሴዕ ባለትዳር የነበረና ሚስቱምጎሜርበመባልእንደምትታወቅ ተገልጿል (ሆሴ2)፡፡ ሆሴዕና ጎሜር በትዳር ሕይወታቸው ኢይዝራኤል፣ ሎሩሐማ እና ሎዓሚ የሚባሉ ሁለትወንዶችናአንድሴትልጅወልደዋል (ሆሴ2-9)፡፡ ጎሜር ባለቤትዋ ነቢዩ ሆሴዕ ትታ ከውሽማዋ ጋር ትኖር በነበረ ጊዜ በእግዚአብሔር ትእዛዝ አማካኝነት ሆሴዕ ወደ ጎሜር በመሄድ በዐሥራአምስትብርናበመቶኀምሳኪሎገብስገዝቶ በድጋሚ ወደ ቤቱ እንደመለሳት ይናገራል (ሆሴ1)፡፡ በእርግጥ ይህንን የሆሴዕ ሚስት ለትዳርዋ ታማኝ ባትሆንም ነቢዩ አባብሎ ወደ ቤትዋ እንድትመለስ የማድረጉን ሂደት በመጠቀም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ስለነበረው መሆኑን ከትንቢቱ ቃል እንረዳለን (ሆሴ 2 14-23)፡፡

የነቢዩሆሴዕልጆችስምየተሰየሙትእግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡ስሞቹምየየራሳቸውየሆነየሚያስተላልፉትመልእክትአላቸው፡፡በዚህምመሠረትኢይዝራኤልእግዚአብሔርይዘራልሎሩሀማምሕረትየለምወይምአለምሕረትሲሆንሎዓሚደግሞሕዝቤአይደለምማለትንያመለክታሉ፡፡

  • የትንቢተ ሆሴዕ ጥንቅር ምን ይመስላል? የመጽሐፉ ጠቅላላ ይዘት በምን ዓይነት መልኩ ይገለጻል?

የመጽሐፉ ይዘት ስንመለከት ሦስት የተለያዩ ነገር ግን ተያያዥነት ያላቸው ክፍሎች ያካተተ መሆኑን እንረዳለን፡፡ የመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል ከሆሴ ምዕራፍ 1  እስከ ምዕራፍ 3 በአመንዝራዪ የነቢዩ ሚስት ጎሜር የተመሰለችው እስራኤል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሆሴዕ አመንዝራዪቱ ሚስትና ልጆች ምሳሌነት በመጠቀም እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግኑኝነት በማስረዳት የእስራኤል ሕዝብ እንደ ጎሜር አመንዝራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ሁለተኛው ክፍል ሆሴ ከምዕራፍ 4 እስከ ምዕራፍ 13 የሚሸፍን ሲሆን የተመረኮዘውም የአባትን ልጅ ፍቅር መሠረት አድርጎ ነው፡፡

እስራኤል እንደ እግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ከእግዚአብሔር አባቱ ጋር ያለው የጠበቀ ወዳጅነት እየገለጸ ይህ ልጅ ግን ከመታዘዝ ይልቅ ዐመፃን እንደመረጠና መታዘዝን እምቢ እንዳለ ያስገነዝባል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ክፍል እግዚአብሔር በሕዝቡ፣ በመሪዎች፣ በካህናቶችና በነቢያቶች ላይ የሚሰነዝረው ወቀሳ፣ ሊመጣ ስለሚችለው ጥፋትና ቅጣት ተፈራርቀው የተገለጹበት ቦታ ነው፡፡ የመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍል የሆነው ሆሴ 14 ላይ የሚያተኩረው ንስሓና የእግዚአብሔር ምሕረትን ነው፡፡ ይህም በነቢዩ ሆሴዕ ጠያቂነት የእስራኤል ሕዝብ መጸጸትና ንስሓ መግባትን ያሳያል፡፡በዚህምምክንያትእግዚአብሔርለሕዝቡምሕረትእንዳደረገናአዲስሕይወትለመስጠትቃልእንደገባያረጋግጣል፡፡

  • ነቢዩ ሆሴዕ በትንቢት ቃሉ ውስጥ እግዚአብሔር ምን ዓይነት አባት ወይም ጌታ በሚመስል መልኩ ገልጾታል? የእግዚአብሔርና የእስራኤል ወዳጅነትስ በምን ዓይነት መልኩ ገልጾታል?

ነቢዩ ሆሴዕ እግዚአብሔርን በተለያየ መልኩ እየገለጸው ሕዝቡ እንዲረዱትና የበለጠ እንዲያውቁት ለማድረግ የተለያዩ ነገሮች በመጠቀም ይገልጻል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እግዚአብሔር እንደ አፍቃሪና ተንከባካቢ አባት (ሆሴ 111)፣ ፈዋሽ አባት (ሆሴ 144)፣ ተንከባካቢ እረኛ (ሆሴ 135) እንደሆነ የሚገልጹትን ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ይህ እግዚአብሔር ለመፍረድና ለመቅጣት በወሰነ ጊዜ ወጥመዱን ዘርግቶ የሚያጠምድ አደገኛ አዳኝ(ሆሴ 712)፣ የሚቦጫጭቅ ድብ፣ የሚሰባብር አንበሳና የሚገነጣጥል አውሬ (ሆሴ 514፤ 128)፣ በመንገድ የሚያደባ ነብርና(ሆሴ 137) እንደሚያጠፋ ብልና ነቀዝ (ሆሴ 512) እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እግዚአብሔር ራርቶ ሕዝቡን በሚያድንበት ጊዜም በደረቅ ምድር እንደሚወርድ ዝናብና (ሆሴ 145) እንደ ለመለመ ዛፍ ጥላ እንደሆነ በተለያየ መልኩ ነቢዩ ይገልጸዋል (ሆሴ 148)፡፡ እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን እስራኤልንም ጭምር በሚኖረው መንፈሳዊ ሕይወትና ለትእዛዛት በሚደርገው ተገዢነት በተለያየ መልኩ እየገለጸ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡

በዚህም መሠረት እስራኤል ሥነ ምግባር የተሞላ ሕይወት ይኖር በነበረበት ወቅት ብዙ ዘለላ እንደያዘ የወይን ተክል (ሆሴ 101)፣ በበረሓ እንደበቀለ የወይን ፍሬና በመከር መጀመሪያ ላይ እንደበሰለች ፍሬ (ሆሴ 910) መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ነገር ግን በኃጢአቱ ምክንያት መጸጸትን እንቢ በማለት በእልኸኛነት ከእግዚአብሔር በሚርቅበት ጊዜ በጽኑ እንደታመመ በሽተኛ (ሆሴ 513)፣ እንደ ርግብ ሞኝና አእምሮ የጐደለው(ሆሴ 711)፣ እንደ እልኸኛና እምቢተኛ ጊደር (ሆሴ 416)፣ የሚወለድበት ጊዜ ሲቃረብ ከእናቱ ሆድ መውጣት እንደማይፈልግ እልኸኛ ሕፃንና (ሆሴ 1313) እንደማይጠቅም ያልተገለበጠ ቂጣ (ሆሴ 78) ሆኖ ተገልጿል፡፡ እስራኤላውያን ተጸጽተው ወደ እግዚአብሔር በሚመለሱበት ጊዜ ደግሞ እንደ አበባ የሚፈኩ፣ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ሥር የሚሰዱና መልካም መዓዛ የሚሰጡ (ሆሴ 145-7) እንዲሁም መልካም ሚስት ሆነው እንደሚኖሩ ነቢዩ ይናገራል(ሆሴ 219)፡፡            

          በአጠቃላይ ትንቢተ ሆሴዕን በደንብ ለመረዳት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የገባው ቃል ኪዳንና በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ትእዛዛት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ እግዚአብሔር በሰጣቸው ትእዛዛት መሠረት በኖሩ ቁጥር ብዙ በረከት እንደሚያገኙና በአንጻሩ ደግሞ ትእዛዛቱን በጣሱና በራሳቸው ፈቃድ መኖር በሚመርጡበት ጊዜ እርግማንና ቅጣት እንደሚደርስባቸው የሚያረጋግጥ ትንቢታዊ ቃል ነው፡፡

  • በመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል ነቢዩ ሆሴዕ ስለ ራሱ ሕይወትና ጎሜር ተብላ ስለምትጠራው አመንዝራዪቱ ሚስቱ ይናገራል፤ ነቢዩ ሆሴዕ የትዳር ሕይወቱን ተጠቅሞ ማስተማር የፈለገው ነገር ምንድን ነው?

በመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ነቢዩ የግል ቤተሰባዊ ሕይወቱን በመጠቀም የእስራኤላውያንን ሕይወት እየዳሰሰና እግዚአብሔር ስለእነርሱ ያለው ጽኑ ስለሆነውና በምንም ዓይነት ሁኔታ ስለማይናወጠው ፍቅር ይናገራል፡፡ ጎሜር በትዳር ሕይወት ውስጥ ከነቢዩ ሆሴዕ ጋር ተሳስራና ልጆች አፍርታ በፍቅር ትኖር ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበረው የማኅበረሰባቸው አኗኗር እንደምንረዳው ባል ለሚስቱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡ በሙሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ የማድረግ ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ከዚህም በላይ የቤተሰቡ ጠባቂና መሪ ስለነበር በቤተሰቡ እጅግ በጣም ይከበርና ይፈራም ነበር፡፡ በአንጻሩ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶችና የሙት ልጆች ተከላካይና ጠባቂ እንደሌላቸው ይቈጠሩ ስለነበር መብታቸው በቀላሉ በሌሎች ተገፈው፣ ፍትሕ አጥተውና ተጐሰቋቁለው ይንከራተቱ ነበር፡፡ ለዚህም ነው እነ ነቢዩ ኢሳይያስ ገና ከነቢይነታቸው አገልግሎት ጅማሬ ስለ እነዚህ ሰዎች ፍትሕ ደጋግመው ሲናገሩና ሲሟገቱ የነበረው (ኢሳ 117)፡፡

በብሉይ ኪዳን ውስጥ በብዙ ቦታዎች ጣዖት ማምለክና አመንዝራነት በተያያዘ መልኩ ይጠቀሳሉ፡፡ ይህም ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን በመጣስ ወደ ሌሎች አማልክት በመሄዳቸው ምክንያት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በማድረግ እስራኤላውያንን ሲንከባከብና ሲጠብቅ ቢኖርም እስራኤላውያን ግን ገና ጥንት የተሰጣቸውን ትእዛዝ በመዘንጋትና ወደ ሌሎች አማልክት በመሄድ እግዚአብሔርን አሳዝነዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለው ፍቅር አለመለወጡ የነቢዩ የትዳር ሕይወት ምሳሌነት በመጠቀም ይገልጽላቸዋል፡፡

ስለዚህ ነቢዩ ሆሴዕ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ከውሽማዋ ጋር በማመንዘር ላይ ወደነበረችውን ወደ ቀድሞዋ ሚስቱን በመሄድ እንደገና ፍቅር ያሳያታል፡፡ ይህች ሴት ሰላምና ፍቅር የተሞላበት የሞቀውን የትዳር ሕይወቷን በመተው ነበር “ወደ ውሽሞቼ እሄዳለሁ፤ እነርሱ ምግብና ውሃ ከሱፍና ከቀጭን ሐር የተሠራ ልብስ፣ የወይራ ዘይትና የወይን ጠጅ ይሰጡኛል” በማለት ኮብልላ የነበረችው (ሆሴ 25)፡፡ ይህንንም በመከተል እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ ወደ ሌሎች አማልክት ዘወር ቢሉም፣ የዘቢብ መሥዋዕት ለጣዖቶች ለማቅረብ ቢፈልጉም እኔ አሁንም እንደምወዳቸው አንተም ሚስትህ ውደዳት በማለት ይነግረዋል (ሆሴ 31)፡፡ ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ራሱ እስራኤልን እንደገና ወደ በረሓ እወስዳታለሁ፤ እዚያም በፍቅር ቃል አባብዬ እማርካታለሁ በማለት ለምሕረትና ለፍቅር ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል (ሆሴ 214)፡፡

በአጠቃላይ ትንቢተ ሆሴዕ ከምዕራፍ 1 እስከ 3 ላይ የጎሜርአመንዝራነትበምሳሌነትበመጠቀምየእስራኤልሕዝብ የገቡትን ቃል ኪዳን በመጣስ ከእግዚአብሔርመንገድእንደራቁናወደጣዖታትእንዳመሩበመግለጥለአምላካቸውለእግዚአብሔርያላቸውንታማኝነትእንዳጎደሉካስገነዘበ በኋላ የእግዚአብሔር ፍቅር በሰዎች የደካማነትና የኃጢአተኛነት ሕይወት የማይቀየር፣ ሁሌም ለምሕረት የተዘጋጀና ደግ አባት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡በእርግጥበዘጸ 3415 ላይወደጣዖታትእንዳይሄዱበደንብተነግሯቸውእነርሱምተስማምተውጉዞጀምረውነበር፡፡አሁንግንሕዝቡከእግዚአብሔርጋርየገቡትንቃልኪዳንጥሰዋል፤ወደጥፋትምመንገድአምርተዋል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሕዝቤ ውለታዬን ዘንግተው ዐምፀዋል በማለት እንዲቀጡ ወይንም እንዲጠፉ አልወሰነባቸውም፤ ይልቅስ ዳግመኛ ወደ ቤቱ እንዲመለሱ የነቢዩ ሆሴዕ የትዳር ሕይወት ምሳሌነት በመጠቀም መንገዱን ያመቻችላቸዋል፡፡

  • ከነቢያት መካከል ስለ እግዚአብሔር መሐሪነትና ይቅር ባይነት በስፋት ከጻፉት መካከል ነቢዩ ሆሴዕ አንዱ ነው፤ ለመሆኑ ነቢዩ ሆሴዕ በምን ዓይነት መልኩ ነው ስለ እግዚአብሔር መሐሪነትና ይቅር ባይነት የገለጸው?

ከትንቢተ ሆሴዕ አስተምህሮቶች ውስጥ ትልቁን ቦታ ይዞ የሚገኘው እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ርኀራኄ፣ ፍቅርና ይቅር ባይነቱን ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅንና ታማኝ ስለሆነ የማያቋርጥ ፍቅርና ምሕረት ለሕዝቡ እንደሚያሳይ፣ ሕዝቡንም በምድሪቱ ላይ አሠማርቶ እንደሚያጽናና እንዲበለጽጉም እንደሚያደርጋቸው ያስገነዝባል (ሆሴ 2 19-23)፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገውን መሥዋዕት ወይም ቁርባን ሳይሆን የተጸጸተና ለንስሓ የተዘጋጀ ልብ መሆኑን በተለያየ መልኩ ደጋግሞ ይገልጻል፡፡ እኔ ከመሥዋዕት ይልቅ ፍቅርን እወዳለሁ፤ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እመርጣለሁ በማለት ከምንም በላይ ፍቅርን፣ በፍቅር የታነጸና የተጸጸተ ልብ እንደሚወድ ይናገራል (ሆሴ 6 6)፡፡ እንደ ነቢዩ ሆሴዕ አገላለጽ ርኁርኁነት፣ መሐሪነትና ይቅርባይነት የእግዚአብሔር ባሕርይ ሲሆኑ ቁጡነት፣ ቂም በቀልነትና የጥፋት መንፈስ የሰዎች ባሕሪዎች ናቸው፡፡ ይህንንም ሲገልጽ የቁጣዬን መቅሠፍት አላመጣም፤ ዳግመኛም እስራኤልን አላጠፋም፤ ምክንያቱም እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁም፤ እኔ ቅዱስ ነኝ፤ በመካከላችሁም እገኛለሁ፤ በቁጣዬም ወደ እናንተ አልመጣም ይላል (ሆሴ 11 8)፡፡  

እግዚአብሔር ሕዝቡን ገና ከጥንት ጀምሮ እያፈቀረ፣ እያስተማረና ይቅርታ እያደረገ ቢንከባከባቸውም እነርሱ ግን ከእርሱ ከመራቅ፣ ለጣዖታት መሥዋዕት ከማቅረብና ለምስሎቹም ዕጣን ከማጠን አልተቈጠቡም፤ ይህም ሆኖ ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ መራቅን ወይም እነርሱ ላይ ጥፋት እንዲመጣ መፍቀድ ሳይሆን ለምሕረትና እነርሱን ዳግመኛ በፍቅር ለመቀበል የተዘጋጀ መሆኑን ያስገነዝባቸዋል (ሆሴ 11 1-4)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር የማይናወጥና የማይሻር እንዲያውም ሕዝቡን ከከዳተኝነታቸው ፈውሶ ወደ ራሱ የሚመልስ፣ በሙሉ ልብ የሚወድ፣ ዳግመኛ አዲስ ሕይወት በመስጠት በራሱ ጥላ ሥር የሚያኖራቸውና ቁጣውንም የሚያርቅ አምላክ እንደሆነ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ያስገነዝባል (ሆሴ 14 4-8)፡፡ እግዚአብሔር መቼውንም ቢሆን ሕዝቡን የማይረሳ፣ የማይጥልና አሳልፎ የማይሰጥ መሆኑን ሲያስረዳ እስራኤል ሆይ እንዴት እጥልሃለሁ? እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? ለአንተ ያለኝ ፍቅር ታላቅ ስለሆነ ይህን ሁሉ እንዳደርግ ልቤ አይፈቅድልኝም ይላል (ሆሴ 11 8)፡፡

  • ነቢዩ ሆሴዕ ስለ እውነተኛ ንስሓ ያስተማረው በምን መልኩ ነው? እንደ ነቢዩ ሆሴዕ አገላለጽ እውነተኛ ንስሓ ማለት ምን ማለት ነው?

ነቢያቶች የሕዝቡን ኃጢአት እየገለጡ ሕዝቡ አካሄዱን እንዲቀይርና በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ አዲስ የሕይወት ጉዞ እንዲጀምር በተደጋጋሚ ያስተምራሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ነቢዩ ሆሴዕ ሕዝቡ የፈጸሙትን ኃጢአቶች በመዘርዘር በሙሉ ልባቸው ተጸጽተው ንስሓ በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ተደጋጋሚ የሆነ ጥሪ አድርጐላቸዋል፡፡ ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ፍቅር እጅግ በጣም የበዛና የማይናወጥ ቢሆንም ሕዝቡ ግን ለእግዚአብሔር ያላቸው ፍቅር እንደ “ማለዳ ጉምና እንደ ጠዋት ጤዛ” ፈጥኖ ይጠፋል(ሆሴ 6 4)፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ተሳሳተ የሕይወት ጐዳና ይሄዳሉ፤ እግዚአብሔርንም ያሳዝናሉ፡፡ እግዚአብሔር ካዘነባቸው የሕዝቡ ኃጢአቶች ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ሕዝቡ ከእንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቃሉ፤ የጥንቆላ ዘንግ ይጠቀማሉ፤ ዝሙት ይፈጽማሉ፤ በተራራ፣ ታላላቅ በሆኑና ቅርንጫፋቸው በተንሰራፋ ጥላማ ዛፎች ሥር መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሕያው እግዚአብሔር በማለት በስሙ ይምላሉ እንዲሁም ግፍና ግድያ ይፈጽማሉ(ሆሴ 4 11-19)፡፡

ስለዚህ ነቢዩ ሆሴዕ ወደ እውነተኛ ንስሓ ሲጠራቸው ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ አሰናክሎ የጣላችሁ የገዛ ኃጢአታችሁ መሆኑን ዕወቁ፤ ይላቸዋል(ሆሴ 14 1)፡፡ በተጨማሪም ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ምሕረትን በመማጸን እንዴት ንስሓ መግባት እንዳለባቸው ሲነግራቸው ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ በምሕረት ተቀበለን፤ በቃል ኪዳናችንም መሠረት የከንፈራችን ፍሬ የሆነውን ምስጋና እናቀርብልሃለን በማለት ጸልዩ፤ ይላቸዋል(ሆሴ 14 2)፡፡ ከዚህም በላይ ነብዩ ሕዝቡ “መጠጊያ የሌለን ሕዝቦችህን ማረን” በማለት እግዚአብሔርን ከልብ በመማጸን እንዲለምኑትና እውነተኛ ንስሓ እንዲገቡ መንገዱን ያመቻችላቸዋል(ሆሴ 14 3)፡፡ በእርግጥ ለነቢዩ ሆሴዕ የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፤ ጻድቃን ይሄዱበታል፤ ኃጢአተኞች ግን ይሰናከሉበታል(ሆሴ 14 9)፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ወደ ጻድቃን ሕይወት ተመልሰው፣ እውነተኛ ንስሓ ገብተውና ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው ቅን በሆነው መንገድ እንዲመላለሱ በተደጋጋሚ ይጠራቸዋል፡፡

የነቢዩ የንስሓ ጥሪ የሰማው ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ያቅዳል፡፡ ሕዝቡ እንዲህ ይላል ኑ! ወደ እግዚአብሔር እንመለስ! እርሱ እንደሰበረን እርሱ ይፈውሰናል፤ እርሱ እንዳቈሰለን እርሱ ቁስላችንን ይጠግናል፤ ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፤ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን (ሆሴ 6 1-2)፡፡ ሕዝቡ በአፉ ይህን ቢልም የልብን ሁሉ መርምሮ የሚያውቀው እግዚአብሔር ግን ንስሓቸው እውነተኛ ስላልነበር ተቃወማቸው፡፡ እንዲያውም “ከእንግዲህ ወዲያ ለእነርሱ ፍቅር አላሳያቸውም” በማለት በኃጢአታቸው ምክንያት ታላቅ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ያሳውቃቸዋል(ሆሴ 9 15 እና 10 10)፡፡ ነገር ግን ይህ ሕዝብ ተጸጽቶ በሙሉ ልቦና ወደ እግዚአብሔር ከተመለሰ በኃጢአቱ ምክንያት መቅሠፍትም አይመጣበትም፤ በኃጢአቱ ምክንያት ወደ ሙታን ዓለም ከመውረድ ይድናል(ሆሴ 12 14)፡፡

  • ነቢዩ ሆሴዕ ካህናትና ነገሥታቶች የገሠጻቸው ለምንድን ነው?

ካህናቶች ራሳቸው በቅድስና እየኖሩ በቤተ መቅደስ ሆነው መሥዋዕት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንመምራትየእግዚአብሔርሕግናትእዛዛትማስተማርትክክለኛውንመንገድ ለሕዝቡ ማሳየትና ተገቢውን የአምልኮ ሂደት በሚገባ የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እንደ ነቢዩ ሆሴዕ ግን ካህናቶች ይህንን ተግባር መወጣት ስለተሳናቸው እንዲያውም ትእዛዛቱን ስላቃለሉ ካህናት ሆናችሁ እንድታገለግሉኝ አልፈልጋችሁም፤ ትእዛዛቴንም ስላቃለላችሁና ስለረሳችሁ ልጆቻችሁ በእኔ ዘንድ የተረሱ ይሆናሉ ይላቸዋል(ሆሴ 4፡6)፡፡ በእርግጥ ካህናቶች እግዚአብሔርን ትተው ሌሎች አማልክት ከማገልገልም አልፈው በዝሙት ራሳቸውን አርክሰዋል(ሆሴ 4፡10)፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው እንደ ተራ ሕዝቦች ሆነዋል(ሆሴ 4፡9)፡፡ ስለዚህ ካህናቶች ክብራቸው ተገፎ ይዋረዳሉ፤ በብርቱም ይቀጣሉ(ሆሴ 4፡9)፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩ ነገሥታቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ ስላልተወጡ እነሱም በእግዚአብሔር ቁጣ ይጠፋሉ በማለት ይናገራል፡፡ ጥንት ምንም ዓይነት ነገሥታት ባልነበሩበት ወቅት ሕዝቡ በጠየቀው መሠረት የሚመሩአቸው ነገሥታትና መሳፍንቶች ተሰጥቶአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነዚህ ነገሥታት ሕዝቡን መከላከልና መምራት ተሳናቸው፤ ስለዚህ እነሱም ይጠፋሉ፤ በጦርነት ከባድ ጥቃት ይደርስባቸዋል(ሆሴ 10፡15 ፤ 12፡9-11)፡፡ በኋላም ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ነገሥታትን አነገሡ፤ መሳፍንትን መርጠው ሾሙ(ሆሴ 8፡4)፤ ነገር ግን የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ከማሟላት ውጪ ምንም ሊፈይዱ ስላልቻሉ ከፍርድና ከቅጣት አያመልጡም(ሆሴ 5፡1-3)፡፡ በአጠቃላይ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር እንዲርቅና በተሳሳተ የሕይወት መንገድ እንዲጓዝ ካህናቶች፣ ነቢያቶችና የሕዝብ መሪዎች ታላቅ ሚና ስለተጫወቱ ከመጠየቅና ከመፍረድ አያመልጡም፡፡

  • ሕዝቡ በኃጢአታቸው ምክንያት በእግዚአብሔር እንደሚቀጡ ነቢዩ ሆሴዕ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ ከሕዝቡ የቅጣት ጊዜ በኋላ ስለሚኖረው የሕዝቡ ሕይወት በምን ዓይነት መልኩ ይገልጸዋል?

ሕዝቡ ትእዛዛቱን ጠብቀው ስላልኖሩና በኃጢአታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ፊት ስለኮበለሉ በብርቱ እንደሚቀጡና ቅጣቱም በቶሎ እንደሚከናወን ነቢዩ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ከዚህ የቅጣት ጊዜ በኋላ እግዚአብሔር ዳግመኛ ራርቶ ሕዝቡን እንደሚጎበኝ ነቢዩ የትንቢት ቃሉን ያሰማል፡፡ ይህ እንዲከናወን ግን ሕዝቡ በንስሓ መመለስና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ኑ! ወደ እግዚአብሔር እንመለስ! እርሱ እንደሰበረን እርሱ ይፈውሰናል፤ እርሱ እንዳቈሰለን እርሱ ቁስላችንን ይጠግናል፤ ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል፤ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን” በማለት “አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን በሚፈልጉበት ጊዜ መልካም የሆነውን ስጦታውን ይቀበላሉ (ሆሴ 6፡1-3)፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስራኤል እግዚአብሔርን እውነተኛው አምላኳ መሆኑን በደንብ ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ እየኖረ መመስከር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ እንደገናም ባሌ ብላ ትጠራኛለች እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ባዓል ብላ በጣዖትዋ ስም አትጠራኝም፡፡ ዳግመኛም የባዓልን ስም እንድትጠራ አልፈቅድላትም በማለት ይናገራል (ሆሴ 2፡16-17)፡፡ ይህንን መናገር ብቻ ሳይሆን ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፤ ለእኔም ታማኝ በመሆን የሚገኘውን በረከት ትሰበስባለችሁ፤ እነሆ ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነው! እኔም መጥቼ በረከቴን አዘንምላችኋለሁ በማለት ያስጠነቅቃቸዋል (ሆሴ 10፡12)፡፡ ያኔ እግዚአብሔርም ይቅር እንደሚላቸው ከማረጋገጡም አልፎ ዳግመኛ የቁጣው መቅሠፍት እንደማያመጣና እስራኤልንም እንደማያጠፋ ቃል ይገባል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር ታላቅ ነውና(ሆሴ 11፡8-9)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ለሕዝቡ በደረቅ ምድር እንደሚወርድ ዝናብ ይሆናል፤ ሕዝቡም እንደ አበባ ይፈካሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባዎችም ሥር ይሰድዳሉ፡፡ አዲስ ሕይወትና ዕድገት ያገኛሉ፤ እንደ ወይራ ዛፍ የሚያምሩ ይሆናሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባም መልካም መዓዛ ይሰጣሉ፤ የበረከታቸውም ሁሉ መገኛ እግዚአብሔር ይሆናል(ሆሴ 14፡4-8)፡፡

  • ነቢዩ ሆሴዕ አመንዝራዪቱ ሚስቱ ዳግመኛ ወደ ቤቱ እንዲመልሳት በተነገረው መሠረት የእግዚአብሔር ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ እርስዋ ሄደ፤ በዐሥራ አምስት ብርና በመቶ ኀምሳ ኪሎ ገብስ ገዛኋት ይላል፡፡ ይህ ሰውን በገንዘብ የመግዛት ክንውን ምንን ያመለክታል?

ይህ ምሳሌአዊ አገላለጽ ነው፡፡ አመንዝራዪቱ ሚስቱ ምናልባት ዐሥራ አምስት ብርና መቶ ኀምሳ ኪሎ ገብስ የሚያህል ዕዳ ነበረባት፤ ነቢዩም የነበረባትን ዕዳ ሁሉ ለአሠሪዋ ከፍሎ ነፃ አደረጋት፤ ፍቅሩንም አሳያት፤ ወደ ቤቱም አምጥቶ በፍቅር ተንከባከባት፡፡ እግዚአብሔር የሰዎችን ዕዳ ሁሉ የሚተው፣ ስለ ሰዎች ዕዳ መሥዋዕት የሚከፍል፣ ከአስከፊው ሕይወት ነፃ የሚያወጣና ዳግመኛ ፍቅሩን እየገለጸ የሚንከባከብ አባት መሆኑን ለመግለጽ የተጠቀመበት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ 

  • ትንቢተ ሆሴዕ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በምን ዓይነት መልኩ ተጠቅሶ እናገኘዋለን?

ትንቢተ ሆሴዕ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ከሁሉም በፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ምሕረት በሚያስተምርበት ጊዜ እግዚአብሔር ከሰዎች የሚፈልገው “ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን” እንዳልሆነ ሲገልጽ ትንቢተ ሆሴዕን ይጠቅሳል (ማቴ 9፡13፤ 12፡7፤ ሆሴ 6፡6)፡፡ የዮሴፍና የማርያም ከሕፃኑ ኢየሱስ ጋር ወደ ግብጽ ያደረጉት ሽሽት ቅዱስ ማቴዎስ ትንቢተ ሆሴዕ ውስጥ የተጻፈውን “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የሚለውን የትንቢት ቃል እንዲፈጸም እንደሆነ ይገልጻል(ማቴ 2፡15 ፤ ሆሴ 11፡1)፡፡

በሌላ መልኩ ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ የአዲስ ኪዳን በር ለሁሉም ማለትም ለአይሁዳውያንና ለአረማውያን እኩል የመከፈቱን ምሥራች ሲያበስሩ ትንቢተ ሆሴዕ በመጥቀስ ነው “በነቢዩ በሆሴዕ እንዲህ እንደተባለ ነው” በማለት የሚናገሩት (ሮሜ 9፡25-26፤ ሆሴ 2፡23 1 ጴጥ 2፡10)፡፡ በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ሲያስተምር በተለይም በክርስቶስ ኃይል ሞት ድል መነሣቱን ሲገልጽ ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኃይል የት ነው? በማለት ከትንቢተ ሆሴዕ ይጠቅሳል (1 ቆሮ 15፡55፤ ሆሴ 13፡14)፡፡ በአጠቃላይ ትንቢተ ሆሴዕ ትኩረት ከሚሰጣቸው ዐቢይት ትምህርቶቹ ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ የገቡትን ቃል ኪዳን ጠብቆ መኖርን ስለሆነ ይህንን መሪ ቃል በአዲስ ኪዳንም ሆነ ዛሬ በምንኖረው ክርስቲያናዊ ሕይወት ትልቅ ቦታ ይዞ የሚገኝና ሁሌም ወቅታዊ ሆኖ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ 

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ፤ 

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

  1. ከሚከተሉት ውስጥ የነቢዩ ሆሴዕ ሕይወትና የትንተ ሆሴዕ መጽሐፍ ይዘት በተመለከተ ትክክለኛውን ምረጥ⁄ምረጪ፡፡

ሀ) ነቢዩ ሆሴዕ የኖረው እስራኤል ውስጥ ጥሩ የሆነ ሥነ ምግባራዊ ሕይወትና ፍትሐዊ የሆነ የአስተዳደር በሰፈነበት ወቅት ነው፡፡ ለ) የነቢዩ ሆሴዕ ሚስት ጎሜር ታማኝ የትዳር ወዳጅ ነበረች፡፡ ሐ) ሆሴዕና ጎሜር በትዳር ሕይወታቸው ኢይዝራኤል፣ ሎሩሐማ እና ሎዓሚ የሚባሉ ሦስትወንድልጆችወልደዋል(ሆሴ2-9)፡፡ መ) ትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 14 የሚያተኩረው ንስሓና የእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ነው፡፡ ሠ) ሎሩሀማማለት “ምሕረትይደረጋል” ማለት ነው፡፡

  1. ነቢዩ ሆሴዕ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና መሐሪነት በተለያየ መልኩ ይገልጻል፡፡ የእግዚአብሔር ማንነት ሲገልጽም የተለያዩ ስሞች ይጠቀማል፡፡ ከዚህ አኳያ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ) እግዚአብሔር ፈዋሽ አባትና ተንከባካቢ እረኛ ነው፡፡ ለ) እግዚአብሔር የሚቦጫጭቅ ድብ፣ የሚሰባብር አንበሳና የሚገነጣጥል አውሬ ተደርጎ ተገልጿል፡፡ ሐ) እግዚአብሔር ከሕዝቡ መሥዋዕትንና ቁርባንከሕዝቡ የሚፈልግ አምላክ ነው፡፡መ) እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር የማይናወጥና የማይሻር ነው፡፡ ሠ) እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዳግመኛ አዲስ ሕይወት በመስጠት በራሱ ጥላ ሥር የሚያኖራቸውና ቁጣውንም የሚያርቅ አምላክ ነው፡፡

  1. ነቢዩ ሆሴዕ ስለ እውነተኛ ንስሓ ከተናገረው ውስጥ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ) ንስሓ እስከሆነ ድረስ ሁሉንም የንስሓ ድርጊቶች እግዚአብሔር ይቀበላል፡፡ ለ) ሐረዝቡ ተጸጽቶ በሙሉ ልቦና ወደ እግዚአብሔር ከተመለሰ በኃጢአቱ ምክንያት ወደ ሙታን ዓለም አይወርድም፡፡ ሐ) ለነቢዩ ሆሴዕ ንስሓ ማለት በካህን ፊት መጥቶ መናዘዝ ነው፡፡ መ) እስራኤላውያን ኑ! ወደ እግዚአብሔር እንመለስ! እርሱ እንደሰበረን እርሱ ይፈውሰናል፤ እርሱ እንዳቈሰለን እርሱ ቁስላችንን ይጠግናል፤ ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፤ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን በማለታቸው እግዚአብሔር ንስሓቸው ተቀበለ፡፡ ሠ) ሕዝቡ የገዛ ኃጢአታቸው አሰናክሎ ጥሎአቸዋል፡፡

  1. ነቢዩ ሆሴዕ ካስተማረው ትምህርት የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው? (ይህንን ለመመለስ ሆሴ ከምዕራፍ 1 እስከ ምዕራፍ 5 በአስተውሎት ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ) ነቢዩ ሆሴዕ ዘማዊት ሴት አግብቶ ሴሰኞች የሆኑ ልጆች እንዲወልድ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ተሰጠው፡፡ ለ) እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዳግመኛ ስለሚያሳየው ፍቅር ሲገልጽዳ በረሓ እወስዳታለሁ፤ እዚያም በፍቅር ቃል አባብዬ እማርካታለሁ ይላል፡፡ ሐ) ነቢዩ ሆሴዕ አመንዝራዪቱ ሚስቱን በዐሥራ አምስት ብርና በመቶ ኀምሳ ኪሎ ገብስ ገዛት፡፡ መ) የካህናት ቁጥር በበዛ መጠን በደላቸውም በእግዚአብሔር ፊት እየበዛ ሄደ፡፡ ሠ) የእስራኤል ሕዝብ ምንም ነገር ሊሰጡት ወደማይችሉ መንግሥታት ዕርዳታ ለማግኘት ፊቱን ስላዞረ ብዙ በረከት አግኝቶአል፡፡

  1. በትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 6 ውስጥ አንድ ትልቅ ትምህርት ሰጭ የሆነ ዓረፍተ ነገር ይገኛል፡፡ ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህ ጥቅስ ምን ይላል? በአዲስ ኪዳን ውስጥ የት ቦታ ተጠቅሶ ይገኛል? ምላሹ ሆሴ 6 በሚገባ ካነበቡ በኋላ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ሙሉ ዓረፍተ ነገሩ መጻፍና በአዲስ ኪዳን ውስጥ የት እንደሚገኝ ጥቅሱ ማሳወቅ ይገባል፡፡
  1. እግዚአብሔር በነቢዩ ሆሴዕ የትዳር ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ከመጽሐፉ እንረዳለን፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ ትታው በመሄድ በምንዝር ሕይወት ውስጥ ትኖር የነበረችውን የቀድሞ ሚስቱ በድጋሚ እንዲያገባት በተነገረው መሠረት የእግዚአብሔር ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ቤቱ አመጣት፡፡ ለሚስቱም ሴሰኛነትሽንና ከሌሎች ጋር ማመንዘርሽን ትተሽ ከእኔ ጋር ለብዙ ቀናት በንጽሕና ኑሪ፤ እኔም በታማኝነት ከአንቺ ጋር እኖራለሁ አላት(ሆሴ 3፡3)፡፡ እያንዳንዳችን በነቢዩ ሆሴዕ ቦታ እናድርግ፤ ዛሬ በሕይወታችን ተመሳሳይ ነገር ቢከሰትና እንደ አስታራቂ ሽማግሌ የሚሆን ሰው መጥቶ ወዳጅህን⁄ ወዳጅሽን ይቅር በለው⁄ ይቅር በዪው፤ ዳግመኛ በቤትህ⁄ በቤትሽ ተቀበዪው ቢለን ይቅርታ አድርገን ያንን ሰው ዳግመኛ በፍቅር ተቀብለን አብረነው በቤታችን እንኖራለንን? ይህንን ለማድረግ መንፈሳዊ ብቃት አለንን? ወይስ ነገሩ ከባድ መስሎ ስለሚታየን ጊዜ ወስደን እናስብበት ይሆን? ወይስ በምንም መልኩ ከዛ ሰው ጋር ለመነጋገር እንኳ አንፈልግም?

እውነተኛ የሆነው ምላሻችን (ለማስመሰል ሳይሆን) ምን ይሆን ነበር? ነገሩ ለምን በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለመመለስ ፈለግን?     

                            

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት