እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የኦሪት ዘፍጥረት ጥናት - ክፍል አንድ

ሚያዝያ 2004 የተልእኮ ትምህርት ሦስት

የኦሪት ዘፍጥረት ጥናት - ክፍል አንድ

Adamo ed Eva በቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ከታሪክና ከዓመታትም አኳያ የመጀመሪያዎች ናቸው ተብለው የሚታወቁት የትኞቹ ናቸው?

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ክፍል ይዘው የሚገኙት የሕግ መጻሕፍት ወይም የሙሴ መጻሕፍት ወይም ደግሞ የኦሪት መጻሕፍት (ብሔረ ኦሪት)  በመባል የሚታወቁትን ነው ፡፡  እነዚህም ፦ ዘፍጥረት ፣ ዘጸአት ፣ ዘሌዋውያን ፣ ዘኊልቅ ፣ ዘዳግም ናቸው ፡፡

ዘፍጥረት ማለት ምን ማለት ነው?

            ዘፍጥረት የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መጽሐፍ ነው ፡፡ “ዘፍጥረት” ከእርሱ ቀጥለው ለሚገኙት መጻሕፍቶች ሁሉ መሠረት ነው ፡፡ ዘፍጥረት የተባለበት ምክንያት ስለ ፍጥረትና የፍጥረት ሁሉ ፍጻሜ ስለሆነው ስለ ሰው ፍጥረት ስለሚናገር ነው ፡፡ ዘፍጥረት ስለ ዓለም አፈጣጠር ፣ ስለ ሰው አፈጣጠር ፣ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ስለመሠረተው ቃል ኪዳንና ሰው በኃጢአት ስለመውደቁ እንዲሁም ስለ ቀደሙት አባቶች አኗኗር ይተርካል ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እንደ ምሳሌው ሲፈጥር ሙሉ ነፃነት ይኖረው ዘንድ እንደወደደ በነፃነቱም ይጠቀም ዘንድ ትእዛዝ እንደሰጠው መጽሐፉ ይናገረናል (ዘፍ 1-2) ፡፡ መጽሐፉ እንደሚከተለው ይከፈላል ፦

  • -    ከምዕራፍ 1-2 ስለ ሥነ ፍጥረት ይናገራል ፡፡
  • -    ከምዕራፍ 3-4 ስለ ሰው ፈተናና ውድቀት ይናገራል ፡፡
  • -    ከምዕራፍ 5-9 የጥፋት ውሃና የኖኅ ቤተሰቦች ድኅነት
  • -    ከምዕራፍ 10-11 የዓለም ሕዝብ ትውልድ ዝርዝርና ቋንቋ መለየት
  • -    ከምዕራፍ 12- 23 የአብርሃም ታሪክ
  • -    ከምዕራፍ 24-26 የይስሐቅ ታሪክ
  • -    ከምዕራፍ 27-36 የያዕቆብ ታሪክ
  • -    ከምዕራፍ 37-50 የዮሴፍ ታሪክ

በዚህ መጀመርያ በሆነው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ፣ ስለ ሰው ፍጥረት ፣ ስለ ዓለም መፈጠርና ስለ ኃጢአት አመጣጥ እናነባለን ፤ ለመሆኑ እግዚአብሔር የሚለው ቃል እንዴት ይገለጻል (እግዚአብሔር ማለት ምን ማለት ነው) ? በኦሪት መጻሕፍት ውስጥ ሌሎች መጠርያ ስሞቹስ የትኞቹ ናቸው?

            እግዚአብሔር የሚለው ቃል የተገኘው ከግእዝ ሲሆን እግዚእ የሚለው ጌታ ማለት ነው ፤ ብሔር ደግሞ ዓለም በሚለው ይተረጐማል ፤ እግዚአብሔር ማለት የዓለም ጌታ ማለት ነው ፡፡

            በዕብራይስጥ እግዚአብሔር የሚጠራባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሦስት ስሞች አሉ ፡፡

1) ኤል ፦ ኃያል (አምላክ) ማለት ነው ፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት “ኤል ወይም ኤሎሂም” የሚለው በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክ ፣ አማልክት ተብሎ ብዙ ጊዜ ተተርጒሟል (ዘፍ 1, 1 ፣ መዝ 81, 9) ፡፡ በዕብራይስጥም ሆነ በሌሎች ሴማውያን ቋንቋዎች የሚናገሩ በእስራኤል አገር በአካባቢዋም ይኖሩ የነበሩ ሁሉ ጣዖቶቻቸውን “ኤል ኤሎሂም” እንደ አማርኛው “አምላክ አማልክት” ብለው ይጠሩአቸው ነበር (ዘጸ 18, 11 ፤ ዘዳ 4, 28) ፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ ቃሉ ገዥነትን ፈራጅነትንም ስለሚያመለክት ሰዎች ተጠርተውበታል (ዘጸ 7, 1 ፣ ዘጸ 21, 6 ፣ መዝ 82, 6 ፣ ዮሐ 10, 34) ፡፡ መላእክትም ተጠርተውበታል (መዝ 8, 5) ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ “ኤል” ከሰውና ከቦታ ስም ጋር ይነገራል ፡፡ ለምሳሌ ኤልሳዕ (እግዚአብሔር ደኅንነት ነው) ኤልሳቤጥ (እግዚአብሔር መሐላዬ ነው) ፣ ቤቴል (የእግዚአብሔር ቤት) ፣ ኤልሻዳይ (ሁሉን ቻይ አምላክ) ማለት ነው (ዘፍ 17, 1) ፡፡

2) ያህዌ ፦ አንዳንዶች ይህንን ስም በተሳሳተ መልኩ በመጥራት የሆቫ ወይም የሆዋ በማለት ሲጠሩት ይሰማል ፡፡ ያህዌ የእግዚአብሔር ስም ነው ፡፡ ትርጓሜውም ያለና የሚኖር እንደ ባሕርዩ የሚሠራ ማለት ነው (ዘጸ 3, 13-15) ፡፡ ያህዌ እግዚአብሔር ተብሎ ተተርጒሟል (ዘፍ 4, 26) ፡፡ ያህዌ ከሌላ ስም ጋር ተዛርፎ ይገኛል ፤ ለምሳሌ ያህዌ ይርኤ ማለት እግዚአብሔር ያያል (ዘፍ 22, 14) ፣ ያህዌ ንሲ (እግዚአብሔር ዓላማዬ ነው (ዘጸ 17, 15) ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የዚህ ያህዌ የሚለው ስም የቃሉ የመጀመሪያው ክፍል “ያህ” ወይንም “ጃህ” ወይንም “ኢያ” የሚለው ቃል “ያህዌ” የሚለውን ይገልጸዋል ወይንም ያህዌ በሚለው ይተረጐማል ፡፡ በዚህም መሠረት የተለያዩ ስሞች ከዚህ ቃል ጋር ተያይዘው እናገኛን ፤ ለምሳሌ ኢዮሳፍጥ (እግዚአብሔር ፈርዷል) ፣ ኢዮራም (እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ) ፣ ኢያሱ (እግዚአብሔር አዳኝ) ፣ ሃሌሉ ሀልሎያህ (እግዚአብሔርን አመስግኑ) ማለት ነው ፡፡ ብዙ ጊዜ ኤልና ያህዌ በአንድነት ይገኛሉ “እግዚአብሔር አምላክ ”ተብለው ይተረጐማሉ (ዘፍ 2, 8)፡፡ ኤልያ ማለት “ያህዌ አምላክ ነው” ማለትን ያሳያል ፡፡

3) አዶን ፦ አዶን ማለት ጌታ ማለት ሲሆን እንደ አንድ የእግዚአብሔር መጠርያ ስምነት ያገለግላል ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ይህንን የዕብራይስጥ ቃል በተለያየ መልኩ ይተረጉመዋል፤ ለምሳሌ ጌታ (መዝ 35, 23) ፣ እግዚአብሔር (መዝ 37, 13) ፣ አቤቱ (መዝ 38, 9) ተብሎ ተተርጒሞአል ፡፡ አዶን ከልዩ ልዩ ስሞች ጋር ተጣምሮ ይገኛል ፤ ለምሳሌ አዶንያስ (ያህዌ ወይም እግዚአብሔር ጌታዬ ነው 2 ሳሙ 3, 4) ፣ አዶኒራም (ጌታዬ ከፍ ያለ ነው 1 ነገ 4, 6) ፡፡ 

እግዚአብሔር የባሕርዩ መገለጫዎች የትኞቹ ናቸው?

            የእግዚአብሔር ባሕሪ መገለጫዎቹ በትክክልና በተረጋገጠ መልኩ ይህ ነው ለማለት ቢያዳግትም እንደ መጽሐፍ ቅዱሳችን አገላለጽ እግዚአብሔር መንፈስ ነው (ዮሐ 4, 24) ፣ ብርሃን ነው (1ዮሐ 1, 5) ፣ ፍቅር ነው (1ዮሐ 4, 8) ፡፡ እግዚአብሔር አካላዊ ወይም እኔነት ያለው ነውና ራሱን በሚገልጥበት መጠን ልናውቀው እንችላለን (ዮሐ 17, 3) ፡፡ ነገር ግን የሚሰጠው መገለጥ በከፊል እንጂ ሙሉ በሙሉ እንድናውቀውና እንድናየው አይደለም (ዘጸ 33, 20 ፣ ኢሳ 55, 8-9 1ጢሞ 6, 16) ፡፡ እግዚአብሔር ስለ ራሱ ብዙ ነገሮች ገልጿል ፡፡ እነዚህም ነገሮች የእግዚአብሔር የባሕርይ መገለጫዎች ይባላሉ ፡፡

የእግዚአብሔር ባሕርይ መገለጫዎች ከተባሉት ውስጥ በፍጥረት ወይም ከፍጡራን ዘንድ ሊገኙ የማይችሉት የትኞቹ ናቸው? 

1) ሁሉን ቻይነቱ ፦ እግዚአብሔር ለባሕርዩ መነሻ ምክንያት የለውም ፤ ከዚህ ተገኘ አይባልም ፡፡ ራሱ በራሱ የነበረ ፣ ያለና የሚኖር ነው ፡፡ “ያህዌ” የሚለው ስሙም ይህን ይገልጣል (ዳን 4, 35 ፣ ዮሐ 5, 26 ፣ ራእ 4, 10-11) ፡፡

2) አለመለወጡ ፦ እግዚአብሔር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ያው ነው ፡፡ አሳቡም አይለወጥም (መዝ 33, 11 ፣ ሚል 3, 6 ዕብ 6, 17) ፡፡

3) አለመወሰኑ ፦ እግዚአብሔር በሁሉ ይገኛል ፤ መጀመሪያና መጨረሻ የለውም (መዝ 145, 3 ፣ 139, 7-10 ፣ ሐዋ 17, 27-28) ፡፡

4) አለመከፋፈሉ ፦ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ የተለየ ነው ፡፡ ሆኖም በፍጥረትም የሚገኘው ሁሉ የእርሱ ሥራ ነው ፡፡ እግዚአብሔር በራሱ መንፈስ ፣ ፍቅር ነው (ዮሐ 4, 24) ፤ ስለዚህ ሰው ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ የባሕርዩ መገለጫ ወደ ሆኑት ወደ ፍቅሩና ወደ መንፈሱ ወደ ጽድቁም ይቀርባል ፡፡

ከዚህ በታች የተጠቀሱት ግን በመጠኑ በፍጥረት (በፍጡራን ዘንድ) ያገኛሉ ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በምልአት ይገኛሉ ፤ በክርስቶስም ተገልጠዋል (1 ዮሐ 1, 14 ፣ ቆላ 2, 9) ፡፡

5) የእግዚአብሔር ዕውቀት ፦ እግዚአብሔር ራሱን (1 ቆሮ 2, 10) ፣ በሰው ልብ ያለውን (ሕዝ 11, 5) ፣ የሚመጣውንም (ኢሳ 46, 10) ያውቃል ፡፡

6) የእግዚአብሔር ጥበብ ፦ እግዚአብሔር ለራሱ ክብር እንዲሆን ሁሉን ያደርጋል (ዳን 2, 20-21 ፣ ሮሜ 11, 33 ፣ 1 ቆሮ 2, 7) ፡፡

7) የእግዚአብሔር ቸርነት ፦እግዚአብሔር ለፍጥረት ሁሉ መልካም ነገርን ያደርጋል (መዝ 146, 8-9 ፣ ማቴ 5, 44-45) ፡፡

8) የእግዚአብሔር ፍቅር ፦ አብ ወልድን ይወዳል (ዮሐ 10, 17) ፣ ዓለምንም ወድዶ ልጁን ሰጠ (ዮሐ 3, 16) ፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በሦስት ቃላት ይገለጻል

-    ጸጋ ፦ በሰው ምክንያት ሳይሆን እንዲሁ በጸጋው እንደሚወድ ያሳያል (ኤፌ 1, 6-7) ፡፡

-    ምሕረት ፦ በኃጢአት ሙታን ስንሆን በምሕረቱ በክርስቶስ ሕይወት ስለሰጠን ፍቅሩን ያሳያል (ኤፌ 2, 4-5) ፡፡

-    ትዕግሥት ፦ ሰዎች እንዲመለሱ በትዕግሥቱ ለንሥሓ ጊዜ በመስጠቱ ፍቅሩን ይገልጣል (ሮሜ 2, 4 ፣ 2ጴጥ 3, 9) ፡፡

9) የእግዚአብሔር ቅድስና ፦ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ የተለየ (ኢሳ 6, 3) በራሱም ንጹህ ነው (ዕን 1, 13) ፡፡

 10) የእግዚአብሔር ጽድቅ ፦ እግዚአብሔር ለሰው እንደ ሥራው ይሰጣል (1ጴጥ 1, 17) ፡፡ ሰውም ለማዳን የኃጢአትን ዕዳ በክርስቶስ በመክፈሉ ጽድቁን አሳየ (ሮሜ 3, 26)፡፡

11)  የእግዚአብሔር ታማኝነት ፦ እግዚአብሔር ታማኝ ነውና (ዮሐ 14, 6) ሐሰትን አይናገርም (ዘኁ 23, 19) ፤ ቃሉንም ይፈጽማል (2ጢሞ 2, 13 ፣ ዕብ 10, 23) ፡፡

12) የእግዚአብሔር ሥልጣን ፦ እግዚአብሔር እንደ ባሕርዩ የፈለገውን ለማድረግ ይችላል (ማቴ 19, 26) ፤ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል (ሮሜ 9, 14-15 ፣ ኤፌ 1, 11) ፡፡

 

ኃጢአት ምንድን ነው? ከፍጥረት አጀማመር ጋር ሲታይ እንዴትስ ወደ ዓለም ሊገባ ቻለ?

ኃጢአት ማለት ስሕተት ፣ ክፋት ፣ ሕግን መተላለፍ ፣ ዓመፃ ፣ በጎ ማድረግን ዐውቆ አለመሥራት ፣ በእምነት መሠረት አለመኖር ፣ ወደ እግዚአብሔር ክብር አለመብቃት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል (ሮሜ 3, 11 ፣ ሮሜ 12, 23 ፣ 14, 23 ፣ 1ዮሐ 3, 4 ፣ ያዕ 2, 10 ፣ ያዕ 4, 17) ፡፡ ሰው ኃጢአተኛ በመሆኑ ፍጹም ደግነትን ማሳየት አይችልም ፣ በራሱም ወደ እውነት ሊመለስ አይችልም ፣ አያስተውልም (1ቆሮ 2, 14) ፣ አይታዘዝም (ሮሜ 8, 7) ፣ አያምንም (ዮሐ 6, 44-45) ፡፡

የመጀመሪያው ሰው አዳም በነፃነቱ ተጠቅሞ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማፍረስ መረጠ ፤ የተከለከለውን ፍሬ ዐውቆ በመብላቱ የእግዚአብሔርን ሥልጣን ተቃወመ ፤ ቸርነቱን ረሳ ፤ ጸጋውን ናቀ ፣ ጥበቡን ነቀፈ ፣ ጽድቁን ካደ ፣ ቃሉንም አቃለለ (ዘፍ 3, 1-6) ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰው ኃጢአተኛ ሆነ ፤ ረከሰ ፤ ልቡም ክፉ ሆነ (ዘፍ 8, 21) ፡፡ ይህንንም በማድረግ ኃጢአት ፣ በኃጢአትም ሞት ወደ ዓለም እንዲገባ አደረገ ፡፡ የአዳም ኃጢአትም በዘሩ ሁሉ ተቈጠረ (መዝ 14, 2-3 ፣ መክ 7, 20 ፣ ሮሜ 5, 12 ፣ 1 ቆሮ 15, 22) ፡፡ 

በኦሪት ዘፍጥረት አገላለጽ መሠረት ሞት ካለ መታዘዝ በመነጨው በኃጢአት ምክንያት የመጣ ነው ማለት ነውን? የሞት አጀማመርና ኃጢአት የተያያዙ ናቸው ማለት ይቻላልን?

            አዎ በእግዚአብሔር መልክ እንደ ምሳሌው በመፈጠሩ ጥንት ለዘለዓለም ነዋሪ የነበረው ሰው ሁሉ መልካሙም ሳይቀር ሁሉም አሁን ሟች እንደሆነ እንረዳለን ፡፡ በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ ፤ ሞት የኃጢአት ውጤት ነው (ሮሜ 5, 12 እና 6, 23) ፡፡ ማስተዋል ያለብን ግን አዳም ትሞታለህ በተባለው መሠረት ወዲያው በሥጋ አልሞተም ነገር ግን ከእግዚአብሔር በመንፈስ ተለየ (ዘፍ 2, 17 ፣ 3, 8 ፣ 19, 22-24)፡፡ ኃጢአት ግን በዓለም ሁሉ ስለተሰራጨ የአዳም ልጅ ነፍሰ ገዳይ ሆነ ፤ በኖኅም ዘመን የሰው ክፋት በምድር ላይ በዛ (ዘፍ 4, 1-6) ፡፡ እግዚአብሔር የጥፋትን ውሃ አዝንሞ ከኖኅና ከልጆቹ በስተቀር የተፈጠረውን ሁሉ አጠፋ (ዘፍ 6, 6-9) ፡፡ የኖኅ ልጆች ግን ከቀደሙት ሰዎች የተሻሉ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፁ ፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ለራሱ የሚሆነውን የተለየ ትውልድ ፈልጎ አብራምን ጠራ (ዘፍ 10-12) ፡፡ ባጠቃላይ በአዳም ውድቀት ምክንያት ኃጢአትና ሞት ወደ ሰው ሁሉ ደረሰ ፡፡

አዳም የሚለው ስም የአንድ ግለ ሰው መጠርያ ስም ብቻ ነው የሚያመለክተው ወይስ ሰዎችን ሁሉ በመወከል የተገለጸ ስም ነው?

            አዳም ማለት ከመሬት የተፈጠረ ማለት ነው ፡፡ ቃሉ ሰውን ወይም ሰዎችን ሁሉ ያመለክታል ፡፡ ከዚህ በላይ ግን የመጀመሪያው ሰው የሚጠራበት ስም ሆነ (ዘፍ 2, 19-25) ፡፡ አዳም በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ (ዘፍ 1, 27) ፤ እግዚአብሔርም እንዲያበጃትና እንዲጠብቃት በኤደን ገነት አኖረው ፡፡ የምድርንም ፍጥረት እንዲገዛ ሥልጣን ሰጠው ፡፡ ስለዚህ እንደ ኦሪት ዘፍጥረት አገላለጽ ፈጣሪ አምላክ ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠረ ፡፡ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ በማለት አንድነታቸውን ባረከ ፡፡ “ብዙ ተባዙ ፤ ምድርንም ሙሉአት ፤ ግዙአትም” አላቸው (ዘፍ 1, 28 ፣ 2, 24) ፡፡ አዳምና ሚስቱ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ ከኤደን ገነት እንዲወጡ ተገደዱ (ዘፍ 3) በማለት አዳም አንድ ሰው ብቻ እንደነበረ ይነግረናል ፡፡

ነገር ግን አዳም አንድ ሰው ብቻ ነው የሚያመለክተው ካልን በታሪኩ ሂደት ላይ አንድ ጥያቄ ያስነሣብናል ፡፡ ይህም አዳምና ሔዋን ሦስት ልጆች እንደነበራቸው ይታወቃል ፡፡ እነዚህም አቤል ፣ ቃየል እና ሴት ነበሩ ፡፡ ቃየል ወንድሙ አቤልን ገደለው (ዘፍ 4, 8) ፡፡ ከዚህ በኋላ ቃየል ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ ሄደ ፤ በዔደን በስተምሥራቅ በሚገኘው በኖድ ምድር ኖረ (ዘፍ 4, 16) ይላል ፡፡ ከዚያም ከሚስቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግኑኝነት አደረገ ፤ እርስዋም አረገዘች ወንድ ልጅ ወለደች ፤ ስሙንም ሔኖክ አሉት (ዘፍ 4, 17) ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ከሆነ ሊነሣ የሚችለው ጥያቄ የቃየል ሚስት ከየት ተገኘች? እግዚአብሔርም ለቃይል እንዲህ አለው “ማንም አይነካህም ፤ አንተን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው ፡፡ ይህ የሚያሳየው በአካባቢው ሌሎች ነዋሪዎች እንደነበሩና በምድር ላይ አዳም ፣ ሔዋንና ልጆቻቸው ብቻ እንዳልነበሩ ያስረዳል ፡፡ ስለዚህ አዳምና ሔዋን የሰውን ፍጥረት ወክለው የተገለጹ የወንድና የሴት አምሳያዎች ናቸው ፡፡ አዳም የሰውን ዘር ወክሎ የሚገኝ መጠርያ ስም ነው፡፡  

ሔዋን ማለት ምን ማለት ነው? በዘፍጥረት አገላለጽ ሔዋን ማን ናት?

            ሔዋን የሕያዋን ሁሉ እናት ማለት ነው ፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ሔዋን የመጀመርያዋ ሴት የአዳም ሚስት ናት ፡፡ እግዚአብሔር ከአዳም ሥጋ ፈጠራት ፤ አዳምም በደስታ ተቀበላት (ዘፍ 2, 20-25) ፡፡ ሰይጣን በእባብ ምሳሌ አታለላትና የተከለከለውን ፍሬ በላች ፤ ፍሬውንም ለአዳም ሰጠች ፡፡ በኋላም ስሕተትዋን በእባቡ አማካኘች (ዘፍ 3, 1-13) ፡፡ በስሕተት ስለወደቀች ለባልዋ እንድትታዘዝ በጭንቅም ልጅ እንድትወልድ ተፈረደባት (ዘፍ 3, 16) ፡፡ አዳም ግን በእግዚአብሔር ቃል ተስፋ አድርጎ ዘር እንደሚኖራት አመነና ሔዋን ብሎ ሰየማት (ዘፍ 3, 15) ፡፡ ስለዚህ ከላይ እንደተገለጸው ሔዋን የሕያዋን ሁሉ እናት ከአዳም ጋር በመሆን ፍጥረትን ሁሉ ወክላ የምትገኝ ነች እንጂ አንዲት ሴት ብቻ (አንዲት ግለሰብ ብቻ) አይደለችም ፡፡

እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረው በኋላ የነበሩ ሰዎች ረጅም እድሜ ይኖሩ እንደነበር ተገልጿል ፤ ለምሳሌ ማቱሳላ ለ969 ዓመታት እንደኖረ ከዘፍጥረት እንረዳለን (ዘፍ 5, 25) ፤ በኋላ ግን የሰው እድሜ ከ70 እስከ 80 ዓመታት ገደማ ተወሰነ ፤ ይህ ለውጥ ለምን ወይም በምን ምክንያት ተከሰተ?

            እድሜ የእግዚአብሔር በረከት ነው (መዝ 91, 16) ፤ እግዚአብሔርን የሚታዘዙ የረጅም እድሜ ተስፋ አላቸው (ዘጸ 20, 12) ፡፡ በእርግጥ በአባቶች ዘመን ሰዎች ብዙ ዓመታት በሕይወት ይኖሩ ነበር (ዘፍ 5 እና ዘዳ 34, 7) ነገር ግን የሰው ዘር በምድር ላይ እየበዛ በሄደ ጊዜ ነገሮች ተለወጡ ፡፡ “የሰው ዘር በምድር ላይ እየበዛ በሄደ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱ ፤ በዚያን ጊዜ ልዩ የሆኑ ፍጥረቶች የእነዚህን ሴቶች ልጆች ውበት ተመለከቱ ፤ ከመካከላቸውም የሚወዱአቸውን እየመረጡ ወሰዱ ፡፡ እግዚአብሔርም ሕይወት ሰጭ የሆነው መንፈሴ ከሰዎች ጋር ለዘላለም አይኖርም ፤ ሰዎች ሟቾች ስለሆኑ ከእንግዲህ ወዲያ ከ120 ዓመት የበለጠ አይኖሩም አለ” (ዘፍ 6, 1-3) ፡፡

እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ የተጸጸተበትና ያዘነበት ጊዜ አለን? በመጸጸቱና በማዘኑስ የፈጠራቸው ፍጥረቶች ከምድር ላይ ለማጥፋት የወሰነበት ጊዜ አለን?

            አዎ እግዚአብሔር በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ ምን ያህል ዐመፀኞች እንደሆኑና አሳባቸውም ዘወትር ክፋት ብቻ እንደሆነ በተመለከተ ጊዜ ሰዎችን በመፍጠሩና በምድር ላይ እንዲኖሩ በማድረጉ አዘነ ፤ እጅግም ተጸጸተ ፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር “እነርሱን በመፍጠሬ አዝኛለሁ ፤ ስለዚህ እነዚህን የፈጠርሁአቸውን ሰዎች ፣ እንስሳት ፣ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና ወፎችንም ጭምር ከምድር ላይ አጠፋለሁ” አለ (ዘፍ 6, 5-8) ፡፡ በኖኅ ዘመን የተከሰተውም የጥፋት ውሃ የዚህ ውጤት እንደነበር ይታወቃል ፡፡

የጥፋት ውሃ ማለት ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር የጥፋት ውሃ እንዲደርስ ለምን ፈቀደ?

            የጥፋት ውሃ ማለት በኖኅ ዘመን 40 ቀንና 40 ሌሊት ያለማቋረጥ የዘነበ ዝናብና በዝናቡ ምክንያት ምድርንም ያጥለቀለቃት ውሃ ማለት ነው ፡፡ ይህ ውሃ ምድርን ሁሉ ለአንድ ዓመት ያህል ሸፍኖት እንደቆየ ይታወቃል ፡፡

የሰው ክፋት ሲበዛ ፣ የልቡ አሳብና ምኞት ሲከፋ እግዚአብሔር ሰውን ሊያጠፋ ወሰነ ፡፡ እግዚአብሔርም ኖኅን እንዲህ አለው “የሰውን ዘር በምድር ላይ ለማጥፋት ወስኛለሁ ፤ ምድር በሰዎች የዐመፅ ሥራ ስለተሞላች ሰዎችን ፈጽሞ ከምድር አጠፋቸዋለሁ” (ዘፍ 6, 13) ፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሰው ዘር በሙሉ ከምድር እንዲጠፋ እግዚአብሔር አልፈቀደም ፡፡ በምድር ላይ የተወሰኑት እንዲቀሩ አደረገ ፡፡

            ኖኅ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ ፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ መርከብን ሠራ ፤ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ ሲመጣ ኖኅ ቤተሰቡና ወደ መርከቡ ያስገባቸው እንስሳት ዳኑ ፤ ሌሎች ግን ጠፉ (ዘፍ 7) ፡፡ ከጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር ዓለምን እንደገና በውሃ እንዳያጠፋ ቃል ኪዳን ሰጠ (ዘፍ 8, 20 – 9, 17) ፡፡ እግዚአብሔርም እንዲህ አለ “ሰው በሚፈጽመው በደል ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን አልረግምም ፤ ምክንያቱም ገና ከሕፃንነቱ ጊዜ ጀምሮ የሰው አሳብ ክፉ መሆኑን ዐውቃለሁ ፤ በአሁኑ ጊዜ እንዳደረግሁት ሕይወት ያለውን ፍጥረት ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አላጠፋም” (8, 21) ፡፡

እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሰጠ ወይም ቃል ኪዳን ገባ ስንል ምን ማለት ነው? ቃል ኪዳኑ ምንን በተመለከተ ነው? ቃል ኪዳን የተሰጣቸው ወይም የተገባላቸውስ እነማን ናቸው?

            ቃል ኪዳን ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ሰዎች ሲስማሙ ነገሩን ለማጽናት ቃል ኪዳን ይገባባሉ ፤ ለምሳሌ ዮናታን ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ገባ (1 ሳሙ 18, 3-4) ፡፡ እግዚአብሔር ዓለምንና ሕዝቡን የሚያስተዳድረው በቃል ኪዳን ሥርዓት ነው ፡፡ በማናቸውም ቃል ኪዳን ውስጥ የቃል ኪዳን ሰጪ ፣ ተቀባይ ፣ የአቀባበል ምልክት ፣ ተስፋ ፣ የተስፋውም ምልክት ይገኛሉ ፡፡ እግዚአብሔር በሰው ደግነት ሳይሆን እንዲሁ በጸጋው ቃል ኪዳንን ፈቅዶ ይሰጣል ፡፡ ሰዎችም ቃል ኪዳኑን ተቀብለው ቢታዘዙለት የቃል ኪዳኑን በረከት ይቀበላሉ ፡፡ ቃል ኪዳኑን ሲቀበሉ እግዚአብሔር ምልክት ያበጃል ፡፡ ይህም የቃል ኪዳኑ ማኅተም ነው ፡፡ እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ውስጥ ላሉት ተስፋና የተስፋ ምልክት ይሰጣቸዋል ፡፡ ስለ ሰው ያለው የእግዚአብሔር አሳብ አይለወጥም ፡፡ ከመጀመርያው ጀምሮ ሰውን በጸጋው ተመልክቷል ፡፡ ከሰው የሚፈለጉት ደግሞ እምነትና መታዘዝ ናቸው ፡፡ እነዚህ ነገሮች ከዘመን ዘመን አይለወጡም ፡፡ ዘመን ሲለወጥ የቃል ኪዳኑ ዋና መሠረት አይሰረዝም (ገላ 3, 15-18) ፡፡ ነገር ግን የአፈጻጸሙ ድርጊት ይለወጣል (2ቆሮ 3, 6-18 ፣ ዕብ 8, 6-13) ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ሰዎች እግዚአብሔር የሰጣቸው ቃል ኪዳኖች እስከነ ምልክቶቻቸው እንደሚከተለው ይቀርባሉ ፦

የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የተሰጠው

ተቀባዮች

የመቀበላቸው ምልክት (ማኅተም)

ተስፋ

የተስፋ ምልክት (ማኅተም)

ለአዳም (ዘፍ 2, 8-17 ፤ ሆሴ 6, 7)

አዳምና ሔዋን

መልካምና ክፉን የሚያሳውቅ ዛፍ

ሕይወት

የሕይወት ዛፍ

ለኖኅ (ዘፍ 9, 1-17)

የዓለም ሕዝብ

 

በምድር መኖር

ቀስተ ደመና

ለአብርሃም (ዘፍ 17, 1-21 ፤ ሮሜ 4, 11)

አብርሃምና ዘሩ

ግዝረት

የአሕዛብ በረከት ፤ የከነዓን ምድር

 

ለሙሴ (ዘጸ 19, 5 ፤ 6, 24 ፤ 7, 8

የእስራኤል ሕዝብ

ሰንበት (ሕዝ 20, 10-17)

ሕይወት በአገራቸው

የፋሲካ መታሰቢያ

በክርስቶስ (ኤር 31, 31-34 ፤ 1ቆሮ 11, 23-26)

በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ

ጥምቀት

የዘላለም ሕይወት

ቅዱስ ቁርባን

 ባጠቃላይ እግዚአብሔር ከአዳም ጋር የሥራ ቃል ኪዳን አደረገ ፡፡ አዳም ቢታዘዝ ኖሮ ለእርሱና ለዘሩ የዘላለምን ሕይወት ያስገኝ ነበር ፤ ባለመታዘዙ ግን የኃጢአትን ፍርድ በእርሱና በዘሩ ላይ አስከተለ (ሮሜ 5, 12-21) ፡፡ ክርስቶስ ሁለተኛው አዳም ስለሆነ በእርሱ ለሚያምኑት ሕይወት አስገኝቶላቸዋል (1ቆሮ 15, 20 እና ከ45-50) ፡፡

የትምህርቱ ዋና አዘጋጅ ፦ አባ ምስራቅ ጥዩ

ረዳት አዘጋጅና መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

ጸሐፊ ፦ ለምለም ክፍሌ (ከሰበካው ሐዋርያዊ ጽ⁄ቤት)

  ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች 

1) የሰውና የፍጥረት እንዲሁም ሰማይና ምድር በውስጥዋም ያ ነገሮች ሁሉ አፈጣጠር በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድና ሁለት ውስጥ ተደጋግሞ ተገልጿል ፡፡ ለመሆኑ እንደ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ አገላለጽ ሰው በስንተኛው ቀን ተፈጠረ ? ምዕራፍ ሁለትስ ውስጥ ሰው የተፈጠረው በመጀመሪያ ነው ወይስ በፍጥረት መጨረሻ ወይስ በፍጥረት መካከል ?

-    _____________________

 -    ____________________

 2) የሰው አፈጣጠር በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድና ምዕራፍ ሁለት ውስጥ የተለያየ ነው ፤ ይህን የሰው አፈጣጠር በተመለከተ ከሚከተሉት ውስጥ ትክክለኛ ያልሆነውን መልስ ምረጥ

ሀ) ዘፍጥረት አንድ ላይ ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳያ ተፈጠረ

ለ) ዘፍጥረት አንድ ላይ እግዚአብሔር ሰዎችን ሲፈጥራቸው ወንድና ሴት አድርጎ ነው

ሐ) ዘፍጥረት ሁለት ላይ እግዚአብሔር ከመሬት ዐፈር ወስዶ ሰውን ከዐፈር አበጀው

መ) ዘፍጥረት ሁለት ላይ እግዚአብሔር በመጀመሪያ አዳም ፈጠረ ፤ ቀጥሎም ከጎኑ አጥንት አንዱን ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራት

ሠ) ሁሉም ትክክል ናቸው

3) እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረው በኋላ በዔደን ገነት አኖረው ፤ ቀጥሎም ሰውን “በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙ ዛፎች ሁሉ ፍሬ ልትበላ ትችላለህ ፤ ነገር ግን ደጉን ከክፉ ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት ከሚሰጠው ዛፍ ፍሬ አትብላ” አለው (ዘፍ 2, 15-17) ፡፡ ሴቲቱም (ሔዋን) እባቡ ፍሬውን ወስዳ እንድትበላ በተናገራት ጊዜ “እግዚአብሔር በአትክልቱ ቦታ መካከል ካለው ዛፍ ፍሬ አትብሉ ፤ በእጃችሁም አትንኩት ፤ ይህን ብታደርጉ ትሞታላችሁ” ብላ መለሰችለት ፡፡ በዚህ ጊዜ እባቡ ሔዋንን ለማሳማን የተናገራት ንግግር ምን ነበር? (ዘፍ 3 አንብብ)  

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት