እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፲፰ - የጥበብ መጻሕፍት ጥናት (መጽሐፈ መክብብ)

ክፍል ሁለት - ትምህርት ዐሥራ ስምንት

የጥበብ መጽሐፍት ጥናት - መጽሐፈ መክብብ

ecclesiastesመጽሐፈ መክብብ በማንና መቼ ተጻፈ? መጽሐፉስ ስለምን ያስተምራል?

          መክብብ ማለት “ሰባኪ” ወይም “አስተማሪ” ማለት ነው ፡፡ በዚህም መጽሐፍ የሚሰብክ ወይም የሚስተምር ንጉሥ ሰሎሞን ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ በእርግጥ ሰባኪው “በኢየሩሳሌም የነገሠ የዳዊት ልጅ” እንደነበር ተገልጿል(1፡ 1፡ 12)፤ ጥበቡም በብዛት ተጠቅሶአል (መክ 1፡ 16፤ 2፡ 9)፤ ምሳሌዎችንም መሰብሰቡ ታውቋል (መክ 12፡ 9 1 ነገ 4፡ 32)፡፡ ሊቃውንት መጽሐፉ ውስጥ ደራሲው የተጠቀመው የዕብራይስጡ አጻጻፍ በማየት ይህ መጽሐፍ የኋላ ዘመን ነው እንጂ የሰሎሞን ዘመን አይደለምና ደራሲው ሌላ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ትምህርቱ ያለ ጥርጥር የሰሎሞን እንደሆነ እነዚሁ ሊቃውንቶች ይናገራሉ፡፡ {jathumbnail off}

ጸሐፊው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ “እግዚአብሔር የሌለበት ሕይወት ከንቱ ነው፤ አያጠግብም ወይም አያረካም” ይላል፡፡ ይህም ማለት እንደ ንጉሥነቱ ሁሉን ሊያደርግ ይችላል፤ እንደ ሀብታምነቱ የወደደውን ሊገዛ ይችላል፤ እንደ ጠቢብነቱ ሁሉን ሊመረምር ይቻለዋል፤ ከእርሱ ይበልጥ የሚችል የለም፤ ነገር ግን ምንም ነገር እግዚአብሔር ያልታከለበት ሕይወት ትርጉም የለውም፡፡ በአጠቃላይ “የሰው ሕይወት ከንቱ ነው”፤ የሰው ሕይወት አጭር ከመሆኑም በላይ ውጣ ውረድና ውዝግብ ፣ የተወሳሰበ ፍርደ ገምድልነትና መታከት የሞላበት ነው ብሎ የደመደመ ጸሐፊ ነው፡፡

መጽሐፉ በመጀመሪያው ክፍሉ መክብብ የተባለው ሰው ከፀሐይ በታች ማለት በዓለም ላይ ሁሉም ዞሮ ዞሮ እንደሚመጣ ፍጻሜም ነገር እንደሌለ አይቶአል(መክ 1)፡፡ የዚህ ዓለም ደስታ የተባለውን ሁሉ ፣ ሣቅን ፣ መጠጥን ፣ ጨዋታን ፣ ሀብትን ፣ ዕውቀትን ፣ ሥልጣንን ፣ ንብረትን ፣ የሴቶችን ፍቅር ፣ ክብርን ፣ ማናቸውንም ነገር ሁሉ ፈትኗል፤ ፈትኖም ሁሉም ከንቱ ፣ ነፋስን እንደመከተልና የማያጠግብ መሆኑን ተገንዝቧል (መክብብ 2)፡፡

ከምዕራፍ 3-11 ባለው ክፍል ውስጥ ሁለት አሳቦች ጐን ለጐን ተብራርተው ይገኛሉ፡፡ በመጀመሪያው እግዚአብሔር በነገሩ ከሌለ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ሞት ከንቱ ነው፤ ሰው እንደሚሞቱ እንስሳዎች ነው (መክ 3፡ 18-21)፡፡ ቀጥሎም ራስዋ ዓለም ውብ ናት፤ የእግዚአብሔርም ፍጥረት ናት፤ ስለዚህ ሰው በዓለም ሳለ ይደሰትባት፤ ተስፋውን ግን አይመሥርትባት (3፡ 11-13)፡፡ በመጨረሻም አጥጋቢ ደስታ ፣ የተትረፈረፈ ሕይወት በዓለማዊ ነገር በማናቸውም በኩል እንደማይገኝ ይገልጻል፡፡ መጽሐፉ “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዙንም ጠብቅ፤ ምክንያቱም ይህ የሰው ዋና ተግባሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስውር የሆነውን ነገር ሳይቀር የሰውን ሥራ ሁሉ ክፉውንም ደጉንም ወደ ፍርድ ያመጣዋል” በማለት ይደመድማል፡፡

ጸሐፊው “ሁሉ ነገር ከንቱ ነው፤ እንዲያውም የከንቱ ከንቱ ነው” ይላል፡፡ ጸሐፊው ሁሉ ነገር ከንቱ መሆኑንና በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ለማብራራት የተጠቀመበት ምሳሌያዊ አገላለጽ ወይም የማረጋገጫ እውነታ ብሎ ያቀረባቸው ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

ጸሐፊው ይህንን በተለያየ መልኩ እያብራራና የተለያዩ ምሳሌዎች በመጠቀም ይገልጻል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በዚህ ምድር አዲስ ነገር እንደሌለ ለማሳየት ከተጠቀማቸው አገላለጾች ውስጥ የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  1. ትውልድ አልፎ ትውልድ ይተካል፤ ምድር ግን ሳትለወጥ ለዘላለሙ ጸንታ ትኖራለች(መክ 1፡ 4)፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ቀድሞም የነበረ ነው፤ ወደፊትም ሌላ ትውልድ ልክ ዛሬ እንዳለነው ሰዎች ዓይነት ይኖራል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ነበሩ፤ አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡
  2. ፀሐይ ወጥታ ትጠልቃለች፤ እንደገናም ወደምትወጣበት ስፍራ ለመድረስ ትጣደፋለች(መክ 1፡ 5)፡፡ ፀሐይ ቀድሞ ነበረች፤ አሁንም አለች፤ ወደፊትም ትኖራለች፡፡ ጠዋት ስትወጣም ሁሌም ከበስተ ምሥራቅ ነው፤ ስትጠልቅም ወደ ምዕራብ ነው፡፡ ሁሌም ተመሳሳይ ነገር ነው፤ በየቀኑ ተመሳሳይ ድርጊት ይደጋገማል፡፡ ስለዚህ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡
  3. ነፋስ ወደ ደቡብም ወደ ሰሜንም ይነፍሳል፤ ዞሮ ዞሮም እንደገና ይለሳል(መክ 1፡ 6)፡፡ ነፋስ ሁሌም የሚነፍስበት አቅጣጫ ተመሳሳይ ነው፤ ይነፍሳል ያቆማል፤ ገናም ይነፍሳል ያቆማል፤ ሁሌም ተመሳሳይ ድርጊት ነው፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡
  4. የወንዝ ውሃ ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳል፤ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ውሃ ተመልሶ እንደገና ወደሚፈልቅበት ወደ ወንዞቹ መነሻ ይሄዳል(መክ 1፡ 7)፡፡ የወንዝ ውሃ በየቀኑ ይፈሳል፤ በተመሳሳይ አቅጣጫ ይወርዳል፤ በመጨረሻም ባሕር ወዳለበት ይደርሳል፡፡ ባሕር ደግሞ ሁሌም በቦታው እንዳለ የወንዝ ውሃ ይቀበላል፤ በቅቶኛል በማለት የወንዙን ውሃ አይመልስም፤ ዝም ብሎ የሚደጋገም ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉን ነገር አሰልቺ ነው፤ አሰልቺነቱም ሰው በቃል ገልጦ ሊናገረው እንኳ አይችልም፤ ዐይን አይቶ አይጠግብም፤ ጆሮም ሰምቶ በቃኝ አይልም(መክ 1፡ 8)፡፡

በአጠቃላይ እንደ ጸሐፊው አገላለጽ ቀድሞ የሆነው ነገር እንደገና ይሆናል፤ አሁንም የሚደረገው ነገር ሁሉ ያው ቀድሞ የተደረገው ነው፤ ስለዚህ በመላው ዓለም አዲስ ተብሎ የሚጠራ ምንም ነገር የለም፡፡ ባለፉት ዘመናት ተደርገው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ የሚያስታውስ የለም፤ ከእነርሱም በኋላ ተከታትለው የሚመጡትም ነገሮች ቢሆኑ በተተኪው ትውልድ ዘንድ መታሰቢያ አይኖራቸውም(መክ 1፡ 9-11)፡፡ ስለዚህም ምንም አዲስ ነገር የለም፤ ሁሉም ከንቱ ነው፡፡

ጸሐፊው “ሁሉ ነገር ከንቱ ነው፤ እንዲያውም የከንቱ ከንቱ ነው” የሚለውን ለማረጋገጥ ራሱ በሕይወት ዘመኑ ያሳለፈውን ሕይወት በመዘርዘር ይናገራል፡፡ እነዚህ እንደ ማረጋገጫ የተጠቀማቸው የራሱ የቀድሞ ሕይወት ዝርዝር ምን ነበር? ምን ዓይነት የሕይወት አኗኗር ከኖረ በኋላ ነው “ሁሉ ነገር ከንቱ ነው” ወደሚለው መደምደምያ የደረሰው?

          ይህንን ለማረጋገጥ ጸሐፊው ቀድሞ የኖረውን ሕይወት በዝርዝር በመተንተን ሁሉም ነገር ከንቱ መሆኑን ለማረጋገጥ ይክራል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡

-       ሳቅ፦ በተለያየ ምክንያት እየሳቀ ሕይወቱን ለማስደሰት ሞከረ፤ ነገር ግን ሳቅ ሞኝነት እንደሆነና ምንም ዓይነት ዘላቂ የሆነ ደስታ እንደማይቸር ተረዳ(መክ 2፡ 2)፡፡

-       ወይን ጠጅ፦ ልቡን በወይን ጠጅ እያዝናና አጭር ዕድሜውን ለመግፋት ሞከረ፤ ነገር ግን ይህም ከንቱ መሆኑን ተረዳ(መክ 2፡ 3)፡፡

-       መኖሪያ ቤት፦ ትልልቅ መኖሪያ ቤቶች በመሥራት ፣ የልዩ ልዩ አትክልትና የፍሬ ዛፍ በዙሪያው በመሥራትና እንደ ገነት አድርጎ በማዘጋጀት እንዲሁም የውሃ ግድቦች በመሥራት ራሱን ለማስደሰት ሞከረ፤ ነገር ግን ይህም ከንቱ መሆኑን ተረዳ(መክ 2፡ 5)፡፡

-       ወርቅና ብር፦ እርሱ ከሚገዛቸው አገር ሁሉ ብዙ ወርቅና ብር በማስመጣት አከማቸ፤ የሚያሞግሡት አዝማሪዎች ሰበሰበ፤ ተድላና ደስታ ሊሰጡ የሚችሉ ብዙ ሴቶችንም ሰበሰበ፤ ነገር ግን ይህንን ሁሉ ከንቱ መሆኑን ተረዳ(መክ 2፡ 8)፡፡

-       ታላቅነት፦ ከእርሱ በፊት ኢየሩሳሌም ውስጥ ከነበሩት ታላላቅ ሰዎች በላይ ሆኖ ለመኖር በሚያስችል መልኩ ሕይወቱን መራ፤ ጥበብም ከእርሱ ዘንድ ጸንታ ኖረች፤ ሰውነቱ የሚያስፈልገውን ደስታ ሁሉ አልነፈገውም፤ ደክሞ ባገኘው ነገር ሁሉ መደሰትን ፈለገ፤ ነገር ግን ይህም ጊዜያዊና ጠፊ መሆኑን ተረዳ(መክ 2፡ 9-10)፡፡ ሁሉም ከንቱ ነው፡፡

በአጠቃላይ ጥበበኞችም ሆንን ሰነፎች ሁላችንም ሞት ይጠብቀናል፤ ሕይወት ትርጉም የላትም፤ በዚህ ዓለም የደከመበትና የለፋበትን ነገር ሁሉ የከንቱ ከንቱ ነው(መክ 2፡ 18)፡፡       

ጸሐፊው አብዛኛው ትኩረቱ “ስለ ሕይወት ከንቱነት” ከሆነ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔር እንዴት ይገለጻል? ከሰው ልጆች ጋር ያለው ወዳጅነት ወይም ግኑኝነት በምን ዓይነት መልኩ ተገልጾ ይገኛል?

-       ከሁሉም በፊት እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ በመወሰን ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ የሠራ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዘላለማዊነትን በሰዎች ልቦና አሳድሮአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሁሉ እስከ መጨረሻው ያውቅ ዘንድ ለሰው የተሰጠው ዕውቀት ሙሉ አይደለም(መክ 3፡ 11)፡፡

-       እግዚአብሔር የሠራው ነገር ሁሉ ዘላለማዊነት አለው፤ እግዚአብሔር ሰዎች እንዲፈሩት አደረገ(መክ 3፡ 14)፡፡

-       እግዚአብሔር ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብን ፣ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጣል(መክ 2፡ 26)፡፡

-       እግዚአብሔር ደስታንና መከራን የሚልክበት ጊዜ ይኖራል፤ የትኛውን ቀድሞ እንደሚመጣ ግን ሰው ማወቅ አይችልም(መክ 7፡ 14)፡፡

-       እግዚአብሔር ለሰዎች ሀብትና ብልጽግና ይሰጣል፤ ለሰው የሰጠውንም ሀብት እንዲደሰትበት ይፈቅድለታል(መክ 5፡ 19)፡፡

-       እግዚአብሔር በሞኞች አይደሰትም(መክ 5፡ 4)፡፡ እግዚአብሔር ስውር የሆነውን ነገር ሳይቀር የሰውን ሥራ ሁሉ ክፉውንም ደጉንም ወደ ፍርድ የሚያመጣ አምላክ ነው(መክ 12፡ 14)፡፡ 

በአጠቃላይ እግዚአብሔር ዘላለማዊ የሆነ ፣ ሁሉንም ነገር የሚመራና የሚያዝ የፍጥረት ሁሉ ባለቤት ነው፤ የሁሉን ፈራጅ ነው፤ ሁሌም መፈራትና መከበር ያለበት አባት ነው(መክ 12፡ 13-14)፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ምድራዊ ሀብትንና ብልጽግናን ክብርንም ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚያስፈልገውም ነገር ሁሉ ምንም አያጐድልበትም(መክ 6፡ 2)፡፡

ጸሐፊው ስለ ሕይወት ከንቱነትና በዚህ ምድር ከፀሐይ በታች ምንም ዓይነት አዲስ ነገር እንደሌለ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በተጨማሪም የሰው ዕድሜ በጣም አጭር መሆኑን አያይዞ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ ሰው አጭር የሆነው ምድራዊ ሕይወቱ በሚኖርበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት ከሚሰጠው ምክር ውስጥ ዋናዎቹን ጥቀስ፡፡

-       እግዚአብሔር ሰዎችን ልበ ቅኖች አድርጎ ፈጥሮአቸዋል፤ እነርሱ ግን ሁሉ ነገር በተንኰል መመራመር አበዙ(መክ 7፡ 29)፡፡

-       ሰው በዚህ ዓለም ሳለ እግዚአብሔር በሰጠው አጭር ዕድሜ የደከመበትን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት መደሰት አለበት፡፡ ሰው በዕድሜው ማጠርና መርዘም ከመጠን በላይ መጨነቅ የለበትም(መክ 5፡ 18፡ 20፤ 9፡ 7)፡፡

-       ክፉ ሰዎች ሁሉ ነገር ስለማይሠምርላቸው ሕይወታቸው እንደ ጥላ ያልፋል፤ ለእግዚአብሔርም ባለመታዘዛቸው ምክንያት ገና በወጣትነት ጊዜአቸው ሕይወታቸው ይቀጫል(መክ 8፡ 13)፡፡

-       ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤት በሚገባበት ጊዜ አረማመዱ በጥንቃቄ ማድረግ አለበት፤ በእግዚአብሔር ቤት መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ የምክር ቃላትን መስማት ይበልጣል(መክ 5፡ 1)፡፡

-       ሰው ከመናገሩ በፊት በደንብ ማሰብ አለበት፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በችኮላ ስእለት ማድረግ የለበትም፤ ተስሎ የማይፈጽመው ከሆነ ጥንቱንም ባይሳል ይሻለው ነበር(መክ 5፡ 2-5)፡፡

-       በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጠቢባን መሆን ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም ጥበብን ማግኘት ርስትን የመውረስ ያህል ነው፤ በገንዘብ እንደሚገኝ ዋስትና ይሆንላቸዋል፤ የዕውቀትም ብልጫዋ ጥበብን ለገበዩ ሁሉ ዋስትናን መስጠትዋ ነው(መክ 7፡ 11-12)፡፡

-       ሰው ባለው ኃይል ሥራውን ሁሉ በትጋት መፈጸም አለበት፤ ምክንያቱም ወደ ሙታን ዓለም ከወረደ በኋላ በዚያ ሥራና አሳብ ፣ ዕውቀትና ጥበብ የለም(መክ 9፡ 10)፡፡

-       ሰው በሥራ መድከሙ የሚበላውን ነገር ለማግኘት ነበር፤ ይሁን እንጂ “በቃኝ” ማለት አያውቅም(መክ 6፡ 7)፡፡

-       በተለይም ወጣቱ ትውልድ በወጣትነቱ ዘመን ደስ ሊለው ይገባል፤ በልቡም ሐሤት ማድረግ አለበት፤ ዐይኑ የሚያየውና ልቡ የሚመኘው ነገር ሁሉ ይፈጽም፤ ሆኖም ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣው ማወቅ አለበት(መክ 11፡ 9)፡፡ ስለዚህ ሰው በወጣትነቱ ዘመን እግዚአብሔር ማሰብ አለበት(መክ 12፡ 1)፡፡

በአጠቃላይ ሰው ለእግዚአብሔር ታዛዥ ከሆነ ሁሉም ነገር ይሠምርለታል(መክ 8፡ 12)፡፡ የሰው ዋና ተግባሩ እግዚአብሔርን መፍራትና ትእዛዛቱንም መጠበቅ ነው፤ ይህ የሰው ዋና ተግባሩ ነው(መክ 12፡ 13)፡፡ ስለዚህ ሰው በሕይወቱ ሳለ መልካም ነገር ከማድረግና ደስ ከሚለው በቀር ሌላ የተሻለ ነገር የለም(መክ 3፡ 12)፡፡

  መጽሐፈ መክብብ ከጥበብ መጽሐፍት ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ መጽሐፈ መክብብ ጥበብንና ጥበበኞችን እንዴት ይገልጻቸዋል?

ጸሐፊው ጥበብን ያወድሳል፡፡ ጥበብ ለሰዎች እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነና ዘወትር በሰዎች መፈለግ ያለበት ትልቁ የሕይወት መምሪያ ቁልፍ ነው፡፡ ከጦር መሣሪያ ይልቅ ጥበብ ትሻላለች(መክ 9፡ 18)፤ ጥበበኛ ሰው መልካምን ነገር ያደርጋል(መክ 10፡ 2)፡፡ ጥበበኛ ሰው በንግግሩ ክብርን ያገኛል፤ ሰነፍ ግን በገዛ ንግግሩ ይጠፋል፤ ምክንያቱም የሰነፍ ሰው ንግግር በስንፍና ተጀምሮ በከባድ እብደት ይደመደማል፤ ሰነፍ ሰው ልፍለፋ ያበዛል(መክ 10፡ 12-14)፡፡ ጥበበኞች ሰዎች መነሻ መድረሻቸው ያውቃሉ(መክ 2፡ 14)፡፡ በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጥበብን ፈልገው ጠቢባን መሆን ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም ጥበብን ማግኘት ርስትን የመውረስ ያህል ነው፤ በገንዘብ እንደሚገኝ ዋስትና ይሆንላቸዋል፤ የዕውቀትም ብልጫዋ ጥበብን ለገበዩ ሁሉ ዋስትና መስጠትዋ ነው(መክ 7፡ 11)፡፡ ጥበብ የተካኑ ጠቢባን ሌሎችን ያስተምራሉ፤ የጠቢባን ንግግር እረኛ የከብቶቹን መንጋ እንደሚነዳበት ጫፉ እንደሾለ በትር ነው፤ በአንድነት የተከማቹ ምሳሌዎች ጠልቀው እንደሚገቡ ምስማሮች ናቸው፤ እነርሱም የሁላችን ጠባቂ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸው(መክ 12፡ 11)፡፡

ጸሐፊው ስለ ክፉና ደግ ሰዎች ሕይወት በመገረም ይናገራል፤ ስለ አኗኗራቸው ሁኔታ እየተደነቀ ይገልጻል፡፡ ለመሆኑ ጸሐፊው ስለ ክፉና ደግ ሰዎች ዕለታዊ ሕይወት በተመለከተ ያስገረመው ነገር ምንድን ነው?

-       ክፉ ሰዎች ሞተው ወደ መቃብር ይወርዳሉ፤ ከመቃብር መልስ ግን በደል የሠሩባት የዚያች ከተማ ሕዝብ ተሰብስቦ ሲያሞግሳቸው በመስማቱ ይገረማል፡፡ በምድራዊ ሕይወት ክፉዎች ከነበሩ ለምን ከሞታቸው በኋላ በሰዎች ይሞገሳሉ?(መክ 8፡ 9-10)፡፡

-       ሰዎች ሆን ብለው ወንጀል ይሠራሉ፤ ስለ ወንጀላቸው ፈጣን የሆነ የቅጣት ፍርድ አይሰጣቸውም፤ ይኸውም ኃጢአተኞች መቶ ጊዜ ወንጀል እየሠሩ ለረዥም ዘመን በመኖራቸው ምክንያት ጸሐፊው ይገረማል፡፡ አግባብ እንደሌለውም ይናገራል(መክ 8፡ 11-12)፡፡

-       በዓለም ላይ ትክክለኛ ፍርድ ሊገኝ በሚያስፈልግበት ቦታ ዐመፅና ግፍ በመብዛቱ ምክንያት ይገረማል(መክ 3፡ 16)፡፡ 

-       በዓለም ላይ አንዳንድ ጊዜ ደጋግ ሰዎች ለክፉ ሰዎች የሚገባውን ቅጣት ይቀበላሉ፤ ክፉ ሰዎች ደግሞ ለደጋግ ሰዎች የሚገባውን ሽልማት ያገኛሉ(መክ 8፡ 8)፡፡ እንደ ጸሐፊው አገላለጽ ይህ አግባብነት የለውም፤ የሰው ሞራል ይነካል፡፡

-       በዚህ ዓለም ሕይወት ሰነፎች ከፍተኛ ሥልጣን ሲያገኙ ባለጸጎች ግን ችላ ተብለው ዝቅተኛ ስፍራ ይዘዋል፡፡ መሳፍንት እንደ አገልጋዮች በእግራቸው ሲሄዱ አገልጋዮች ግን በፈረስ ተቀምጠው ሲጓዙ በማየቱ ምክንያት አግራሞቱን ይገልጻል፡፡ እንደ ጸሐፊው እይታ ይህ ኢፍትሐዊነት የሰፈነበት ሕይወት ነው(መክ 10፡ 5-7)፡፡

-       ሌላው ጸሐፊው የሚያስገርመው ነገር በዚህ ዓለም ውስጥ ፈጣን ርዋጮች ዘወትር በአሸናፊነት አለመወጣታቸው፤ ጀግኖች በጦርነት ድል አለማድረጋቸው፤ ጠቢባን ባለጸግነት የተማሩ ሰዎችም ሀብትን አለማግኘታቸው፤ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች በማዕረግ አለማደጋቸው ነው(መክ 9፡ 11)፡፡

በአጠቃላይ ጸሐፊው በሰዎች የዚህ ዓለም ኑሮና በሚገጥማቸው የኑሮ ዕድል ቢገረምም በአንድ ነገር ግን ያምናል፡፡ ይህም ክፉ ሰዎች ብዙ ክፋት ያቅዳሉ ነገር ግን በሠሩት ክፋት የሚጎዱት ራሳቸውን ነው፡፡ ይህንንም ሲገልጽ “ጉድጓድ የሚቆፍር ሰው ራሱ ይወድቅበታል፤ ቅጽርንም የሚያፈርስ በእባብ ይነደፋል፤ ድንጋይን የሚፈነቅል በፈነቀለው ድንጋይ ራሱን ይጐዳል፤ እንጨትን የሚፈልጥ በፈለጠው እንጨት ይቈስላል” ይላል(መክ 10፡ 8-9)፡፡ ሌላው የደጋግና የጥበበኞች ሰዎችን ሥራ ፣ ፍቅርም ሆነ ጥላቻ በእግዚአብሔር እጅ ነው(መክ 9፡ 1)፡፡ እግዚአብሔር የሚፈራ ሰው ደግሞ ከመከራ ሁሉ በአሸናፊነት መውጣት ይችላል(መክ 7፡ 18)፡፡

እንደ ጸሐፊው አገላለጽ ሁሉ ነገር ከንቱ ከሆነ የሰው ልጅ የመጨረሻ ሕይወት እንዴት ይጠናቀቃል? የሰው ልጅ ነፍስ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

እንደ ጸሐፊው አገላለጽ ሰው ሟች ፍጥረት ነው፡፡ ሰው የቱንም ያል ብዙ ዓመት ቢኖር በዚያው በተሰጠው በዕድሜው ዘመን ሁሉ ደስ ሊለው ይችላል፤ ሆኖም የዚህ ዓለም ነገር ሁሉ ከንቱ መሆኑንና ወደፊት የሚመጣበትን የጨለማ ዘመን ዘላለማዊ ነው(መክ 11፡ 8)፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ጸሐፊው ሰውም ሆነ እንስሳ የተሠሩት ከዐፈር ስለሆነ ሁለቱም ወደ አንድ ቦታ እንደሚሄዱ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣና የእንስሳት ነፍስ ደግሞ ወደ መሬት አዘቅት እንደምትወርድ የሚያውቅ ማንም እንደሌለና የሰው ልጆችና የእንስሳት ዕድል ፈንታ አንድ እንደሆነ ተናግሮ ነበር(መክ 3፡ 19-20)፡፡ ጥበበኞችም ሆንን ሰነፎች ሁላችንም ሞት እንደሚጠብቀንና ከሞትም በኋላ ተረስተን እንደምንቀር ተናግሮ ነበር(መክ 2፡ 16)፡፡ ሰው ሁሉ ራቁቱን እንደተወለደ ባዶ እጁን ተመልሶ ይሄዳል፤ የቱንም ያህል በሥራ ቢደክም ይዞት የሚሄደው ነገር የለም(መክ 5፡ 15)፡፡ በመጨረሻው ክፍል ግን ሰው ወደ ዘላለማዊ መኖሪያው ይሄዳል፤ አልቃሾችም በየመንገዱ እያለቀሱ ይሸኙታል(መክ 12፡ 5)፡፡ ሥጋ ዐፈር ስለሆነ ወደ ዐፈር ይመለሳል፤ ነፍስም ወደ ፈጠራት ወደ እግዚአብሔር ትሄዳለች በማለት የሰው ነፍስ የመጨረሻ መሄጃዋና መድረሻዋ ዘላለማዊ ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ይገልጻል(መክ 12፡ 7)፡፡

ጸሐፊው ከሚገረምባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ በዚህ ዓለም ውስጥ በዕለታዊ ሕይወት የሚታየው የሰነፍ ሰው አኗኗር ነው፡፡ ለመሆኑ ጸሐፊው “ሰነፍ ሰው” የሚለውን እንዴት ይገልጸዋል?

ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው በጥበብ ታንጸው በትጋት እየሠሩ መኖር እንዳለባቸው ጸሐፊው ይገልጻል፡፡ አንድ ሰው ከጎበዘ ከድኽነት ተነሥቶ በአገሩ ላይ ንጉሥ መሆን ይችላል፤ ወይም ከወህኒ ቤት ወጥቶ በዙፋኑ ላይ መቀመጥ ይችላል፤ ነገር ግን በሚሸመግልበት ጊዜ ምክር የማይቀበል ሆኖ ከተገኘ ዐዋቂ ሆኖ በምስኪንነት ከሚኖር ወጣት የተሻለ ሆኖ አይገኝም(መክ 4፡ 14)፡፡ በአጠቃላይ ሰነፍ ሰው እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡

-       ሰነፍ ሰው በሚተላለፍበት መንገድ ሁሉ ያለ አሳብ ይራመዳል፤ ለሰውም ሁሉ ስንፍናውን ያሳውቃል(መክ 10፡ 3)፡፡

-       ጥበበኛ ሰው በንግግሩ እንደሚከብር ሁሉ ሰነፍ ሰው በንግግሩ ይጠፋል(መክ 10፡ 12)፡፡

-       ጥበበኛ መልካም ነገር መሥራቱ ሰነፍም መሳሳቱ የተለመደ ተግባር ነው(መክ 10፡ 2)፡፡ የሞቱ ዝንቦች ተቀምሞ የተሠራውን የዘይት ሽቶ ሊያገሙት እንደሚችል ሁሉ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ታላቅ ጥበብን ያጠፋል(መክ 10፡ 1)፡፡

-       ዕውቀት የጐደለው ሰነፍ ሰው ወደ ከተማ መውጣት ስለሚሳነው በሥራው ይደክማል(መክ 10፡ 15)፡፡

-       የሰነፍ ሰው ንግግር በስንፍና ተጀምሮ በከባድ እብደት ይደመደማል፤ ሰነፍ ሰው ልፍለፋ ያበዛል(መክ 10፡ 13-14)፡፡

-       የሰነፍ ሰው ሳቅ በእሳት ውስጥ እንደሚንጣጣ የቁጥቋጦ እሾኽ ስለሆነ ትርጉም የሌለው ከንቱ ነገር ነው(መክ 7፡ 6)፡፡

-       እጆቹን አጥፎ የሚቀመጥ ሰነፍ ሰው በራበው ጊዜ የገዛ ሥጋውን እንኳ ለመብላት ይገደዳል(መክ 4፡ 5)፡፡

-       በድንቁርና ውስጥ ያሉ ሰነፎች አንተን እያመሰገኑ ከሚዘምሩልህ ይልቅ ጥበበኞች ቢገሥጹህ ይሻላል(መክ 7፡ 5)፡፡

-       ቁጣ የሰነፎች ቂም በቀል መወጫ ነው(መክ 7፡ 9)፡፡

-       ሰነፍ ሰው ሁልጊዜ ስለ አስደሳች ነገር ብቻ ያስባል፤ ብልኅ ግን የሞትንም ነገር ያስባል(መክ 7፡ 4)፡፡ 

  በአጠቃላይ ሰነፎች ጥበብን መፈለግ አለባቸው፤ የነገሮች ትርጉም የሚያውቅ ጠቢብ የሆነ ሰው ብቻ ነው፤ ጥበብም ፈገግታን በመስጠት የጠቈረ ፊቱን ታበራለታለች(መክ 8፡ 1)፡፡ ስንፍና ወይም ድንቁርና አስከፊና ሞኝነት ነው(መክ 7፡ 25)፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

   

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

  1. መጽሐፈ መክብብን በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው?  ሀ) መክብብ ማለት “ሰባኪ” ወይም “አስተማሪ” ማለት ሲሆን በዚህም መጽሐፍ የሚሰብክ ወይም የሚስተምረውም ንጉሥ ሰሎሞን ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ለ) ጸሐፊው የዚህ ዓለም ደስታ የተባለውን ሁሉ ፣ ሣቅን ፣ መጠጥን ፣ ጨዋታን ፣ ሀብትን ፣ ዕውቀትን ፣ ሥልጣንን ፣ ንብረትን ፣ የሴቶችን ፍቅር ፣ ክብርን ፣ ማናቸውንም ነገር ሁሉ ፈትኗል፤ ፈትኖም ሁሉም ከንቱ ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶአል፡፡ ሐ)በመላው ዓለም አዲስ ተብሎ የሚጠራ ምንም ነገር የለም፡፡ ባለፉት ዘመናት ተደርገው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ የሚያስታውስ የለም፤ ከእነርሱም በኋላ ተከታትለው የሚመጡትም ነገሮች ቢሆኑ በተተኪው ትውልድ ዘንድ መታሰቢያ አይኖራቸውም፡፡ መ)ጥበበኞችም ሆንን ሰነፎች ሁላችንም ሞት ይጠብቀናል፤ ሕይወት ትርጉም የላትም፤ በዚህ ዓለም የደከመበትና የለፋበትን ነገር ሁሉ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ሠ)ቀድሞ የሆነው ነገር እንደገና አይሆንም፤ አሁንም የሚደረገው ነገር ሁሉ ቀድሞ አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡
  2. ጸሐፊው ስለ ክፉና ደግ እንዲሁም ስለ ሰነፍ ሰዎች ሕይወት በመገረም ይናገራል፤ ከሚከተሉት ውስጥ እነዚህ ሰዎች በተመለከተ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው? ሀ)ቁጣ የሰነፎች ቂም በቀል መወጫ ነው፡፡ ለ)እጆቹን አጥፎ የሚቀመጥ ሰነፍ ሰው በራበው ጊዜ የገዛ ሥጋውን እንኳ ለመብላት ይገደዳል፡፡ ሐ) በዓለም ላይ ሁል ጊዜ ደጋግ ሰዎች ለክፉ ሰዎች የሚገባውን ቅጣት ይቀበላሉ፤ ክፉ ሰዎች ደግሞ ለደጋግ ሰዎች የሚገባውን ሽልማት ያገኛሉ፡፡ መ) ክፉ ሰዎች ብዙ ክፋት ያቅዳሉ ነገር ግን በሠሩት ክፋት የሚጎዱት ራሳቸውን ነው፡፡ ሠ)ሰነፍ ሰው ሁልጊዜ ስለ አስደሳች ነገር ብቻ ያስባል፡፡
  3. ጸሐፊው በዚህ ዓለም ስላሉ ነገሮች ከንቱነት ምሳሌዎችና ተፈጥሮአዊ ክስተቶች በመጠቀም በተለያየ መልኩ ገልጾታል፡፡ በዚህ ዓለም ስላሉ ነገሮች ከንቱነት ሲገልጽ ከተጠቀመው ውስጥ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው?(መክብብ ምዕራፍ አንድ እስከ ሦስት ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡ ሀ) ጥበብ በበዛ መጠን ደስታ ይበዛል፤ ዕውቀት በበዛ መጠን የተሻለ ሕይወት መኖር ይቻላል፡፡ ለ) ጥበበኛንም ሆነ ሰነፍን ሁለቱንም ለረዥም ጊዜ የሚያሳታውሳቸው አይገኝም፤ ሁሉም ተረስተው ይቀራሉ፡፡ ሐ) ለሰው የሚጠቅመው ነገር ቢኖር ደክሞ በመሥራት ያፈራውን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት ራሱን ለማስደሰት መቻሉ ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው፡፡ መ) በሕይወት ውስጥ ለማዘን ጊዜ አለው፤ ለመደሰትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ እየዘፈኑ ለመጨፈርም ጊዜ አለው፡፡ ሠ) እግዚአብሔር የሠራው ነገር ሁሉ ዘላለማዊነት አለው፡፡
  4. ጸሐፊው ወይም ንጉሥ ሰለሞን ወይም አንዳንዶች እንደሚጠሩት “ፈላስፋው” ስለ ሕይወት ከንቱነት በተደጋጋሚ በመገረም ከተናገራቸው ነገሮችና ለሰው ልጅ ከሚሰጣቸው ጠቃሚ ምክሮች ውስጥ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ⁄ምረጭ፡፡(ይህን ጥያቄ ለመመለስ መክብብ ከምዕራፍ 4 እስከ 8 ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ) ሰው ወደ ኃጢአት እንዳይገባ ለአንደበቱ ከገደብ ያለፈ ነጻነት መስጠት የለበትም፡፡ ለ) በዚህ ዓለም አንድ ሰው ብቻውን ከሚኖር ይልቅ ሁለት ሆኖ ከሌላ ሰው ጋር ተባብሮ ቢኖር የበለጠ ይሻላል፡፡ ሐ) አስጨናቂ ነገር በበዛ መጠን ክፉ ሕልም ይበዛል፡፡ መ) የሴት ወጥመድነት ከሞት ይልቅ የመረረ ነው፤ ሴት በፍቅርዋ ወንዶችን ታጠምዳለች፤ እግዚአብሔር የሚፈራ ሰው እንኳ ከእርስዋ ሸሽቶ መሄድ አይችልም፡፡ ሠ) በምርምር ብዛት እግዚአብሔር የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ማወቅ አይቻልም፡፡

  1. ጸሐፊው በመጽሐፉ የመጨረሻው ክፍል ስለ ጥበበኛ ሰውና ስለ ወጣቶች ሕይወት ይናገራል፡፡ ይህንን በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ፡፡(ይህንን ለመመለስ መክብብ ምዕራፍ 11 እና 12 ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡ ሀ) ጥበበኛ ሰው በንግግሩ ክብርን ያገኛል፡፡ ለ) የሁሉ ነገር ፈጣሪ የሆነ እግዚአብሔር ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ማወቅና መረዳት ይቻላል፡፡ ሐ) ሰው በወጣትነቱ ዘመን እግዚአብሔርን ማሰብ አለበት፤ ይህን ባያደርግ ግን ክፉ ቀን ይመጣበታል፡፡ መ) እግዚአብሔር ስውር የሆነውን ነገር ሳይቀር የሰውን ሥራ ሁሉ ክፉውንም ደጉንም ወደ ፍርድ ያመጣዋል፡፡ ሠ) ጸሐፊው ለወጣት በወጣትነቱ ዘመን ዐይኑ የሚያየውንና ልቡ የሚመኘውን ነገር ሁሉ እንዲፈጽም ይመክረዋል፤ ነገር ግን በመጨረሻው ወደ ፍርድ እንደሚቀርብ ማወቅ አለበት፡፡
  2. ጸሐፊው በተደጋጋሚ ሁሉ ነገር ከንቱ ፣ የከንቱ ከንቱ ነው ይላል፡፡ በእርግጥ ጸሐፊው ዐይኑ ያየውንና ልቡ የተመኘውን ሁሉ ካገኘና ለብዙ ዘመናት ከኖረ በኋላ ነው ወደዚህ መደምደምያ የደረሰው፡፡ ጸሐፊው በእርግጥ በሕይወቱ ብዙ ሠርቶአል፤ ለፍቶአል፤ ሀብት አፍርቶአል፤ ነገር ግን በመጨረሻ የሰው ድካም ሁሉ ከንቱ ነው፤ ንፋስን እንደመጨበጥ ነው በማለት ይቋጫል፡፡    

-    ሰው የዚህን ዓለም ሕይወት ከንቱነት ለመረዳት በመጀመሪያ ምን ማድረግ አለበት ብለህ ታስባለህ?

-    ሰው የዚህን ዓለም ሕይወት ከንቱ መሆኑን ከተረዳ ምን እያደረገ መኖር አለበት ብለህ ታስባለህ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት