እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዓለም ውበት፣ ሥርዓትና ውኅደት

ግዙፉ ዓለም

ethiopia-tree janekurtzግዙፉን ዓለምን በተለያየ መልኩ፣ ዓይነቱና ሥርዓቱ የፈጠረው እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የፈጣሪን ሥራ በምሳሌያዊ መልክ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ተካሄዶ፣ በሰባተኛው ቀን "ዕረፍት" እንደ ተጠናቀቀ መለከታዊ አድርጎ ያቀርብልናል፡፡ የፍጥረትን ርእሰ ጉዳይ በተመለከተ መጽሐፍ ቅድስ ለድኅነታችን በእግዚአብሔር የተገለጡልንን እሴቶች "የመላውን ፍጥረት ውስጣዊ ባሕርይ" እሴትና አደረጃጀት ተገንዝበን ለእግዚአብሔር ምስጋና እናውል ዘንድ ያስተምረናል"

ሕላዌውን በፈጣሪ አምላክ ላይ ያልመሠረተ ከቶ ምንም ነገር አይኖርም፡- ዓለም የተጀመረው የእግዚአብሔር ቃል ከምንም ነገር /ካለመኖር ወደ መኖር/ ሲያመጣው ነው፤ ሕልውና ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ፣ ተፈጥሮ በሙሉና መላው የሰው ልጅ ታሪክ የተመሠረቱት የዓለም መገናኛ የጊዜ መጀመሪያ ከሆነው ከዚህ ጥንተ ሁኔታ ነው፡፡

እያንዳንዱ ፍጥረት ልዩ የሆነ የራሱ በጎነት ፍጽምና አለው፡- ከ "ስድስቱ ቀናት" ሥራዎች እያንዳንዱን "እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ አየ "ተብሏል፡፡ "በፍጥረት ልዩ ባሕርይ ምክንያት፣ ቁሳዊ ሕላዌ የራሱን ጽናት እውነትና ጥራት እንዲሁም ሥርዓትና ሕግ ታድሏል" እያንዳንዱም ፍጡር ከራሱ ሕላዌ በሚመነጭ በራሱ መንገድ የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ጥበብና መልካምነት ያንጸባርቃል፡፡ ስለዚህ ሰው ነገሮችን ከእግዚአብሔር ፍቃድ ውጭ ያለ አግባብ በመጠቀም እግዚአብሔርን ንቆ በራሱና በአካባቢው ላይ አደጋ እንዳያስከትል የእያንዳንዱን ፍጥረት ልዩ መልካምነት ማክበር አለበት፡፡

እግዚአብሔር የፍጥረታትን እርስ በእርስ መደጋገፍ ይፈልጋል፡- ፀሐይና ጨረቃ፣ የጥድ ዛፍና ትንሿ አበባ፣ ንስርና ድንቢጥ ሥፍር ቁጥር የሌለው ልዩነታቸውና አለመመጣጠናቸው ማንም ፍጥረት ራሱን በራሱ እንደማይችል ያሳየናል፡፡ ፍጡራን ሊኖሩ የሚችሉት እርስ በእርስ በመደጋገፍ አንዱ ሌላውን ምሉዕ ለማድረግ አንዱ ሌላኛውን በማገልገል ብቻ ነው፡፡

የዓለም ውበት፡- ዓለም የሥርዓት እና ውሑድነት፣ በፍጥረታት መካከል ያሉት ልዩነቶችና ዝምድናዎች ውጤት ነው፡፡ ሰው እነዚህን እንደ ተፈጥሮ ሕግ ደረጃ በደረጃ ይገነዘባቸዋል፡፡ ተመራማሪዎች አድናቆታቸውን ይቸሯቸዋል፡፡ የፍጥረት ውበት ወሰን የሌለው የፈጣሪን ውበት ያንጸባርቃልና የሰው ልጅን ፈቃድና አዕምሮ ገዝቶ ከበሬታን ማትረፍ ይኖርበታል፡፡

የፍጥረት ቅደም ተከተል፣ አነስተኛ ፍጽምና ካለው አንስቶ የበለጠ ፍጽምና እስከተቀዳጀው ድረስ በ "ስድስቱ ቀናት" የተፈጣጠር ሥርዓት ሂደት ይገለጻል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ሁሉ ይወዳል፤ እያንዳንዱንም ፍጥረት ድንቢጥን እንኳ ሳይቀር ይንከባከባል፡፡ ይሁን እንጂ ኢየሱስ "እናንተ አኮ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ፤" ወይም እንደገና "ታዲያ ከበግ ሰው አንዴት አይበልጥም?"ሉቃስ 12፡6-7፤ ማቴ 12፡12 ብሏል፡፡

በመንፈስ አነሳሽነት የቀረበው ገለጻ የሰው አፈጣጠር ከሌሎች ፍጥረታት በመለየት እንደሚያስገነዝበው፣ ሰው የፈጣሪ ሥራ ጉልላት ነው፡፡ ሁሉም አንድ ፈጣሪ ያላቸውና ሁሉም የክብሩ ተገዥ ከመሆናቸው ሐቅ የተነሣ በሁሉም ፍጥረታት መካከል ኅብረት አለ፤

ጌታ ሆይ፣ በፍጥረታት ሁሉ፣ በተለይም ለቀን ብርሃን በሰጠኸን በእርሱ በወንድም ፀሐይ የተመሰገንህ ሁን፤ ታላቅ ድንቅን የሚያንፀባርቅና፣ የፍጥረታት ሁሉ ልዑል የሆንከውን፣ የአንተን ምልክት የሚሰጠን ምልክት የሚሰጠን ውብ ነገር ነውና...

ጌታ ሆይ፤ በጣም ጠቃሚና ትሑት፣ ክቡርና ድንግል ስለሆነችው፣ ስለእህት ውኃ፣ የተመሰገንህ ሁን...

ጌታዬ ሆይ፣ በወለደችንና በምትመግበን፣ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎችን፣ ያሸበረቁ አበቦችንና ሣሮችን ስለምታበቅለው ስለእኅታችን፣ ስለእናታችን መሬት የተመሰገንህ ሁን፡፡...

ጌታዬን አመስግኑት፤ ባርኩት፤ እያመሰገናችሁም በታላቅ ትሕትና አገልግሉት፡፡

 ሰንበት- የስድስቱ ቀናት ሥራ ፍጻሜ፡- መጽሐፍ ቅዱስ "እግዚአብሔር የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤" "የሰማይንና የምድርን መፍጠር ፈጽሞ፤" እግዚአብሔር በዚህ ቀን "ዐረፈ"፤ ቀደሰው፤ ባረከውም፡፡ እነዚህ በመንፈስ የተጻፉ ቃላት ታላቅ ትምህርትን ያዘሉ ናቸው፡፡

እግዚአብሔር በፍጥረት አማካይነት አማኝ በሙሉ ልብ የሚመካበት መሠረቱን ጣለ፤ ጽኑ ሆነው የሚኖሩትን ሕግጋቱንም ደነገገ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ጽናትና ታማኝነት ምልክትና ዋስትና ናቸውና፡፡ ሰውም በበኩሉ ለዚህ መሠረት ታማኝነቱን ጠብቆ መኖርና ፈጣሪ በውስጡ የጻፋቸውን ሕግጋት ማክበር አለበት፡፡

ፍጥረት የተሠራው ዕለተ ሰንበትን በማሰብ፣ እግዚአብሔርን እንዲያመልክና ለእርሱ እንዲሰግድ ነው፡፡ አምልኮ በፍጥረት ሥርዓት ተዘግቧል፡፡ የአቡኑ ብሩክ ሕግ እንደሚለው፣ ምንም ነገር "ከእግዚአብሔር ሥራ" ማለትም ከአምልኮ መቅደም አይኖርበትም፡፡ ይህ እንግዲህ የሰውን ጭንቅ ትክክለኛ ቅደም ተከተል ይጠቁማል፡፡

ዕለተ ሰንበት የእስራኤል ሕግ ዕምብርት ነው፡፡ ትእዛዛቱን መጠበቅ፣ በፈጥረት ሥራው እንደ ተገለጸው ከእግዚአብሔር ጥበብና ፈቃድ መስማማት ነው፡፡

ስምንተኛው ቀን፡- ለእኛ ግን አዲስ ቀን ነግቶልናል፤ ይኸውም የክርስቶሰ ዕለተ ትንሣኤ ነው፡፡ ሰባተኛው ቀን የመጀመሪያውን ፍጥረት ይፈጽማል፡፡ ስምንተኛው ቀን አዲሱን ፍጥረት ይጀምራል፡፡ በመሆኑም የፍጥረት ሥራ የሚፈጸመው በታላቁ የድኅነት ሥራ ነው፡፡ የመጀመሪያው ፍጥረት ትርጉሙን የሚያገኘውና ከጫፍ የሚደርሰው፣ በሞገሱ ከመጀመሪያው ፍጥረት በሚልቀው፣ በክርስቶስ በሆነው በአዲሱ ፍጥረት ነው፡፡

ምን ጭ:- አዲሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ

Write comment (0 Comments)

የመላእክት ህላዌ

1. መላእክት

የመላእክት ህላዌ የእምነት ሐቅ

የመንፈሳዊያን፣ መጽሐፍ ቅድስ ብዙውን ጊዜ "መላእክት" ሲል የሚጠራቸው ፈቂቃን ፍጡራን ሕላዌ የእምነት ሐቅ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት እንደማያሻማው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ግልጽ ነው፡፡

እነርሱ ማን ናቸው?

ቅዱስ አውጉስጢኖስ ስለነርሱ ሲናገር "መልአክ" የተግባራቸው እንጂ የባህርያቸው ስያሜ አይደለም፡፡ የባህሪያቸውን ስም ከፈለጋችሁ "መንፈስ" ነው፤ የተግባራቸውን ስም ከፈለጋችሁ "መልአክ" ነው፡፡ ከማንነታቸው "መንፈስ"፣ ከተግባራቸው "መልአክ" የሚለውን ስም አግኝተዋል ይላል፡፡ መላእክት በሁለንተናቸው የእግዚአብሔር መልዕክተኞች ናቸው፡፡ "በሰማይ የሚኖረውን አባቴን ፊት ሁል ጊዜ ስለሚያዩ" "ቃሉን የሚፈጽሙ፣ የቃሉን ጽምፅ የሚሰሙ ኃያላን" ናቸው፡፡ ማቴ 18፡1ዐ መዝ. 1ዐ3፡2ዐ

ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንደ መሆናቸው መላእክት ዕውቀትና ፈቃድ አላቸው፡፡ የክብራቸው ሞገስ እንደሚመሰክረው፣ ከሚታዩ ፍጥረታት ሁሉ በፍጽምና የሚልቁ አካላዊና ሞት የሌለባቸው ፍጥረታት ናቸው፡፡

ክርስቶስ "ከመላእክቱ ሁሉ ጋር"

ክርስቶስ የመላእክት ዓለም ማዕከል ነው፡፡ መላእክቱም የእርሱ ናቸው፡፡ "የሰው ልጅ በመላእክቱ ሁሉ ታጅቦ በክብር ሲመጣ ..." ማቴ 25፡31 የእርሱ ናቸው ምክንያቱም በእርሱ ለእርሱ የተፈጠሩ ናቸውና፡፡ "የሰማይና በምድር ያሉት፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት የሆኑ ወይም ጌትነት፣ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው፡፡" ቆላ 1፡16 የማዳን ዕቅዱ መልክተኞች ስላደረጋቸውም ይበልጥ የእርሱ ናቸው፡፡ "ታዲያ መላእክት የሚድኑትን ለማገልገል የሚላኩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑ መንፈሶች አይደሉምን? ዕብ 1፡14

መላእክት ከፍጥረት ጊዜ ጀምሮና በድኅነት ታሪክ ዘመን በሙሉ ነበሩ፤ ይህን ድኅነት ከቅርብ ወይም ከሩቅ አያበሠሩ የመለኮታዊውን ዕቅድ ፍጻሜ እያገለገሉ ኖረዋል፤ ጥቂት ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል፣ ምድራዊውን ገነት ዘግተዋል፤ ሎጥን ጠብቀዋል፤ ሐጋርንና ልጅዋን አትርፈዋል፤ የአብርሃምን እጅ አቆይተዋል፤ በአገልግሎታቸው የእግዚአብሔርን ሕግ አስተምረዋል፤ ሕዝበ እግዚአብሔርን መርተዋል፤ የብዙዎችን መወለድና መጠራትን አብሥረዋል፤ ነቢያትን ረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ ገብርኤል /የመንገድ ጠራጊውን/ የዮሐንስ መጥምቁንና የራሱን የኢየሱስን ልደት አበሰረ፡፡

ከትስብእት እስከ ዕርገት፣ ሥጋ የሆነውን ቃለ ሕይወት በመላእክት ስግደትና አገልግሎት የታጀበ ነው፡፡ እግዚአብሔር "የበኩር ልጁን ልኮ ወደ አለም ሲያስገባ፣ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት ይላል፡፡ "በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን" ሉቃ 2፡14 እያሉ በክርስቶስ ልደት ያዜሙት መዝሙር እስከ ዛሬ በቤተክርስቲያን ውዳሴ ማስተጋባቱን አላቋረጠም፡፡ ኢየሱስን በሕፃንነቱ ጠብቀውታል፤ በምድረ በዳ አገልግለውታል፤ ከጠላቶቹ እጆች ሊያተርፉት ሲችሉ፣ በእሥራኤል እንደደረሰው ሁሉ በአትክልቱ ውስጥ በመከራው ጊዜ አጽናንተውታል፡፡ እንደገና የክርስቶስን ትስብእትና ትንሣኤ መልካም ዜና በማብሰር "ወንጌልን ያስተማሩ" መላእክት ናቸው፡፡ በሚያበሥሩት ክርስቶስ ደግሞ በሚመጣበት እለት፣ በፍርዱ ላይ ሊያገለግሉት ይገኛሉ፡፡

መላእክት በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውሰጥ

እስከዚያው ድረስ መላው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከመላእክት ምስጢራዊና ኃያል እርዳታ ትጠቀማለች፡፡ በሥርዓተ አምልኮዋ ቤተ ክርስቲያን ከመላእክት ጋር በመተባበር ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ በማለት /ሦስት ጊዜ/ ለእግዚአብሔር ትሰግዳለች፡፡ እርዳታቸውንም /በላቲን ሥርዓት "ሁሉን የምትችል አምላክ ሆይ መልአክህ ... እንጸልያለን"፤ በቀብር ሥርዓተ አምልኮ "መላእክት ወደ ገነት ይመሩህ ዘንድ ..." እያለች ትለምናለች፡፡ በተጨማሪም በሲዛንቲናዊ ሥርዓተ አምልኮ በ "ኪሩቤላዊ ውዳሴ" የአንዳንድ መላእክትን፣ በይበልጥም /የቅዱስ ሚካኤልን፣ የቅዱስ ገብርኤልን፣ የቅዱስ ሩፋኤልን የጠባቂ መላእክትን/ መታሰቢያ ታከብራለች፡፡

የሰው ልጅ ሕይወት ከልደት እስከ ሞት በእነርሱ የቅርብ እንክብካቤና አማላጅነት የተከበበ ነው፡፡ "በእያንዳንዱ አማኝ ጐን አንድ መልአክ እንደ ጠባቂና እረኛ ይቆማል" በዚህች ምድር ላይም ክርስተያናዊ ሕይወት በአምላክ አንድ የሆኑትን የመላእክትና የሰው የተቀደሰ ወዳጅነትን ይካፈላል፡፡

Write comment (0 Comments)

4. የፍጥረት ምስጢር - እግዚአብሔር በጥበብና በፍቅር ዓለምን ፈጠረ

4. የፍጥረት ምስጢር - እግዚአብሔር በጥበብና በፍቅር ዓለምን ፈጠረ

እግዚአብሔር ዓለምን በጥበቡ እንደ ፈጠረ እናምናለን፡፡ ፍጥረት የአንዳች ግዴታ፣ በጭፍን የመጣ ዕጣ ፈንታ ወይም የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ፍጥረት በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ መጣ እናምናለን፤ ፍጥረታቱ ሕላዌውን፣ ጥበቡን፣ ቸርነቱን እንዲካፈሉ ፈቃዱ በመሆኑ ያደረገው ነው፡፡ “ሁሉንም ነገር ስለ ፈጠርህ፣ ሁሉም ነገር የተፈጠረውና ሕልውናን ያኘው በአንተ ፈቃድ ነው፡፡” መዝ. 1ዐ4፡24 ስለዚህም ዘማሪው “እግዚአብሔር ሆይ አንተ ብዙ ነገሮችን ፈጥረሃል፤ ሁሉንም በጥበብ አድርገሃል፡፡” ስለዚህ “ጌታ በሁሉም ቸር ነው፤ ለፍጥረታቱ ሁሉ ይራራል” ሲል ያወድሰዋል፡፡

እግዚአብሔር ዓለምን “ከምንም ነገር” ፈጠረ

እግዚአብሔር ለመፍጠር አስቀድሞ የነበረ ነገር ወይም አንዳች እርዳታ እንደማያስፈልገው፤ ፍጥረት ከመለኮታዊ አካል ሊመጣ ግድ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር በፈቃዱ “ከምንም ነገር እንዲሁ” ይፈጥራል፡፡

እግዚአብሔር ዓለምን አስቀድሞ ከነበረ ነገር ካመጣ ያ ምን ያስደንቃል? አንድ አንጥረኛ ካገኘው ነገር ያሻውን እንደሚሠራ፣ እግዚአብሔርም ከምንም ተነሥቶ የፈለገውን በመሥራት ሁሉን የሚችል መሆኑን ያሳያል፡፡

ፍጥረት “ከምንም ነገር” የመምጣቱ እምነት፣ ቃል ኪዳንና ተስፋ የተጣለበት እውነት እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅድስ ይመሰክራል፡፡ አንዲት የሰባት ልጆች እናት ልጆቿን ለሰማዕትነት ስታበረታታ የሚከተለውን ትላለች፡፡

እንዴት በማሕፀኔ እንደ ተፈጠራችሁ አላውቅም፡፡ ሕይወትና እስትንፋስ የሰጠኋችሁ እኔ አይደለሁም፤ በእያንዳንዳችሁ ውስጥ ያሉትን ሕዋሳት በሥርዓት ያቀናጀሁላችሁም እኔ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ ለፈጣሪ፣ የሰውን ልጅ ለፈጠረና የሁሉንም ነገር መጀመሪያ ላቀደ አምላክ ሕጎች መከበር ብላችሁ አሁን ራሳችሁን ስለረሳችሁ፣ በመሐሪነቱ ሕይወትንና እስትንፋስን እንደገና ይሰጣችኋል፡፡ ሰማይንና ምድርን፣ በእነርሱም ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም ነገር እስኪ ተመልከቱ እግዚአብሔር አስቀድመው ከነበሩ ነገሮች እንዳልሠራቸውም እወቁ፡፡ የሰው ልጅም ወደዚህ ዓለም የመጣው እንዲሁ ነው፡፡

እግዚአብሔር ማንኛውንም ነገር ከምንም ነገር መፍጠር ስለሚችል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለኃጢአተኞች ንጹሕ ልብ በመፍጠር መንፈሳዊ ሕይወትን፣ እንዲሁም ለሙታን በትንሣኤ አማካይነት አካላዊ ሕይወትን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር “ለሙታን ሕይወት ይሰጣል፤ የሌሉ ነገሮችንም ወደ መኖር ይጠራል፡፡” እግዚአብሔር በቃሉ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ማፍለቅ እንደቻለ ሁሉ፣  እስካሁን እርሱን ለማያቁትም የእምነት ብርሃን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡

እግዚአብሔር ሥርዓት ያለው መልካም ዓለም ፈጠረ

እግዚአብሔር በጥበብ ስለሚፈጥር፣ ፍጥረቱ ሥርዓት አለው፡፡ “አንተ ሁሉንም ነገር በልክ፣ በቁጥርና በሚዛን ደልድለሃል፡፡” ጥበብ 11፡2ዐ በዘላለማዊው ቃልና በእርሱም አማካይነት “በማይታየው የእግዚአብሔር አምሳል” የተፈጠረው ዓለም “በእግዚአብሔር አምሳል” ለተፈጠረውና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ለተጠራው ለራሱ ለሰው ልጅ የታሰበና የቀረበ ነው፡፡ የመለኮታዊ እውቅት ብርሃን ተጋሪ የሆነው ሰብአዊ ማስተዋል፣ በፈጣሪና በሥራው ፊት በሚያሳየው ትህትና አክብሮት ካልሆነ በቀር በቀላሉ የሚደርስበት ባይሆንም፣ በፍጥረቱ አማካይነት እግዚአብሔር የሚነግረንን መዳት ይቻላል፡፡ ፍጥረት ከእግዚአብሔር ቸርነት የመጣ በመሆኑ፣ ያን ቸርነት ይጋራል “እግዚአብሔርም የፈጠረውን ሁሉ አየ … እጅግ መልካም መሆኑንም ተመለከተ”  ፍጥረት ለሰው ዘር እንደ ስጦታ እንዲቀርብ፣ ውርሱ እንዲሆንና በአደራ እንዲጠብቀው እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኗልና፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች፣ ቤተ ክርስቲያን ግዙፉን ዓለም ጨምሮ ስለ ፍጥረት መልካምነት፣ ስትከራከር ቆይታለች፡፡

እግዚአብሔር ከፍጥረት ሁሉ የላቀ ቢሆንም፣ ለእርሱ ቅርብ ነው፡፡

እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ደረጃ ከሥራዎቹ ሁሉ የላቀ ነው፡፡ “ለአንተ የሚቀርበው ምስጋና ከሰማይ በላይ ከፍ ያለ ነው፡፡ በርግጥ የእግዚአብሔር “ታላቅነት ሰው ከሚያስተውለው በላይ ነው፡፡” መዝ 145፡3 ነፃና ሥልጣኑ የመላ ፈጣሪ፣ ሕልው ለሆነው ነገር ሁሉ ቀዳሚው መንስኤ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ውስጣዊ ማንነት ግልጽ ነው፡፡ “ሕይወት የምናገኘውና የምንቀሳቀሰው፣ የምንኖረውም በእርሱ ነው፡፡” የሐ.ሥ 17፡28 በቅዱስ አውግስጢኖስ ታላቅ እግዚአብሔር “እጅግ ጥልቅ ከሆነው እኔነቴ በላይ ጥልቅ ከላቀው ከፍታዬም በላይ ከፍ ያለ ነው፡፡”

እግዚአብሔር ፍጥረትን ይቀብቃል፣ ደግፎ ያኖራል

ፍጥረትን በተመለከተ፣ እግዚአብሔር ፍጥረታቱን በራሳቸው አይተዋቸውም፡፡ የሚሰጣቸው ሕላዌና ሕይወት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሰዓትም ይጠብቃቸዋል፤ በሕልውና ያቆያቸዋል፤ ለመሥራት ያስችላቸዋል፤ ከፍጻሜም ያደርሳቸዋል፡፡ ለፈጣሪ አክብሮት በመስጠት የቱን ያህል የእርሱ ድጋፍ እንደሚያሻን መገንዘብ የጥበብና የነጻነት፣ በራስ የመተማመንና የደስታ ምንጭ ነው፡፡

“ሕልው የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ትወድዳለህ፤ ከሠራሀቸው ነገሮች አንዳቸውንም ስንኳ አትጠላም፤ አንተ ብትጠላው ያን ነገር አትፈጥረውም ነበርና፡፡ አንተ ባትፈቅደውማ የቱስ ነገር ቢሆን በፊትህ እንዴት በጸና ነበር? አንተስ ያልወደድኸው ነገር እንደምን ሊዘልቅ ይቻለዋል? ሕያዋንን የምትወድ ጌታ ሆይ! ያንተ ስለሆኑ ሁሉንም ነገሮች ትጠብቃቸዋለህ” ጥበብ 11፡24-26 

Write comment (0 Comments)

ሰማይና ምድር

ሰማይና ምድር

የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት እግዚአብሔር "የሰማይና የምድር ፈጣሪ" ነው በማለት ሲገልጽ፣ የኒቂያ ጸሎት ሃይማኖት ደግሞ፣ ይህ የእምነት መግለጫ "የሚታዩና የማይታዩትን ሁሉ" እንደሚያጠቃልል ያብራራል፡፡

"የሰማይና ምድር" የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ፣ የሚኖር ሁሉ፣ ፍጥረት በሙሉ ማለት ነው፡፡ በፍጥረት ውስጥ ያለውን ትስስር፣ ሰማይንና ምድርን አንድ የሚያደርጋቸውንና እንዲሁም አንዱ ከሌላው የሚለይበትን ሁኔታም ይጠቁመናል፡፡ "ምድር" የሰው ልጆች ዓለም ስትሆን፣ "ሰማይ" ወይም "ሰማያት" ጠፈርንና የራሱን የእግዚአብሔርን "መኖሪያ" "በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ" በሚለም ሐረግ የላቀ የክብር ቦታ የሆነውን "ሰማይ" ሊያመለክትም ይችላል፡፡ በመጨረሻም "ሰማይ" የሚለው ቃል ቅዱሳንና በእግዚአብሔር ዙሪያ የሚገኙ የመንፈሳዊ ፍጥረታትንና የመላእክትን "ቦታ" ያመለክታል፡፡

የአራተኛው ላተራን ጉባኤ /1215/ የእምነት መግለጫ፣ እግዚአብሔር "ከዘመን መጀመሪያ አንስቶ በአንድ ጊዜ ከምንም የስነ ፍጥረትን ሁለቱንም ሥርዓቶች፣ መንፈሳዊንና ምድራዊውን፣ ቀጥሎም ከመንፈስና ከአካል በመሠራቱ፣ የሁለቱም ሥርዓቶች ተካፋይ የሆነውን ሰው መፍጠሩን ያረጋግጣል፡፡

Write comment (0 Comments)

3. “ዓለም የተፈጠረው ለእግዚአብሔር ክብር ነው”

3. “ዓለም የተፈጠረው ለእግዚአብሔር ክብር ነው”

መጽሐፍ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያን ትውፊት “ዓለም የተፈጠረው ለእግዚአብሔር ክብር ነው” የሚለውን መሠረታዊ እውነት ከማስተማርና ከማክበር ወደ ኋላ አይልም፡፡ ቅዱስ ቦናቬንቱራ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው “ክብሩን ለመጨመር ሳይሆን ክብሩን ለማሳየትና ለማሳወቅ ነው” በማለት ያስረዳናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍቅሩንና ደግነቱን ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ለመፍጠር ምንም ምክንያት የለውም፡፡ “ፍጥረታት ሕልውና ያገኙት የፍቅር ቁልፍ እጁን በከፈተ ጊዜ ነው፡፡” የመጀሪያው የቫቲካን ጉባኤ ይህንኑ ጉዳይ ሲያብራራ

ይህ አንድና እውነተኛ አምላክ በራሱ ደግነትና “ሁሉን በሚችል ኃይል” የራሱን ብፅዕና ከፍ ለማድረግ ወይም ፍጹምነት ለማግኘት ሳይሆን ለፍጥረታት በነፃ ፈቃዱ በሚሰጠው ጥቅም አማካይነት ይህን ፍጹምነቱን በግለጽ ለማሳየት ነው፡፡ “ከዘመናት መጀመሪያ አንስቶ ሁለቱንም ዓይነት ፍጥረታት፣ መንፈሳዊውንም ሥጋ ለሳሹንም ከምንም ነገር /እንዲሁ/ ሠራ …” ይላል፡፡

የእግዚአብሔር ክብር ዓለም የተፈጠረለትን ይህን ክስተት እውን ማድረግና ደግነቱን ማስተማርን ያካትታል፡፡  “በፍቅሩም እግዚአብሔር በጐ ፈቃዱ ሆኖ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ ወሰነን፡፡ ይህንንም ያደረገው በተወደደው ልጁ አማካይነት በነፃ የሰጠን ክቡር ጸጋ እንድመሰገን ነው፤” ኤፌ 1፡5-6 ምክንያቱም “የእግዚአብሔርን ክብር በሕይወት ያለ የሰው ዘር ነው፤ የእግዚአብሔር መገለጥ በፍጥረት አማካይነት በምድረ ላይ ላሉ ፍጥረታት ሁሉ ሕይወትን ካስገኘ፣ ሥጋ በሆነው ቃል አማካይነት የአብ መገለጥ እግዚአብሔርን ለሚያዩ ከዚህ የቱን ያህል የላቀ ሕይወት ይሰጣቸዋል፡፡” የፍጥረት የመጨረሻው ግብ እግዚአብሔር “የሁሉም ነገር ፈጣሪ በአንድ ጊዜ የራሱን ክብርና የእኛንመ ብፅዕና በማረጋገጥ መጨረሻ ላይ ሁሉ በሁሉ መሆኑ ነው፡፡”

Write comment (0 Comments)

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት