ሆሳዕና
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Saturday, 16 April 2011 21:58
- Written by Super User
- Hits: 4011
- 16 Apr
ሆሳዕና
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሌላ ቀን እንደ ተራ ሰው ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ይገባ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ግን የአይሁድ ንጉሥ ሆኖ በክብር ገባ፡፡ ከቢታንያ ተነሥቶ ደብረ ዘይት ሲደርስ ከሐዋርያቱ ሁለቱን በቤተፋጌ ሰው ተቀምጦባት የማያውቅ ውርንጭላ እንዲያመጡለት ላካቸው፡፡ “በፊታችሁ ወዳለችው ሀገር ሂዱና ሰው ተቀምጦባት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ፡፡ ባለቤቶቹ ቢጠይቋችሁ ጌታችን ፈልጓት ነው በሏቸው” አላቸው፡፡ ማቴ.21፡1-17
ወደ ቤተፋጌም ሄደው አህያዪቱን አገኙአት፡፡ ሲፈቱአትም ሳለ ባለቤቶቹ መጡባቸውና አስቆሟቸው፡፡ እነርሱም ኢየሱስ እንደፈለጋት ነገሩአቸው፡፡ ባለቤቶቹ ይህንን ሲያውቁ ተውአቸው፡፡ ሐዋርያትም የአህያዪቱን ውርንጭላ ፈትተው ወደ ኢየሱስ ወሰዱ፡፡ አጠገቡም ሲደርሱ ልብሳቸውን በአህያዪቱ ውርንጭላ ላይ አንጥፈው ኢየሱስን አስቀመጡት፡፡
“የጽዮን ልጅ ሆይ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ይመጣል” ዘካ.9፡9 የሚለው የዘካርያስ ትንቢት ተፈጸመ፡፡ ሕዝቡም ኢየሱስ በመምጣት ላይ እንዳለ ሲያውቅ ሊቀበለው ወጣ፡፡ አንዳንዶች ያልፍበት በነበረ መንገድ ልብሳቸውን እንዳንዶቹ ደግሞ የዘንባበ ዝንጣፊ ያነጥፉ ነበር፡፡ ከፊትና በኋላ ያሉት ደግሞ “ሆሳዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ በታላቅ ድምፅ ይጮሁ ነበር፡፡ ኢየሱስ በሕዝቡ እልልታና ደስታ ታጅቦ ሲገባ ተጠንቅቀው ይታዘቡትና ይመለከቱት የነበሩ ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርቱን ዝም እንዲያሰኛቸው ተናገሩት፡፡ እርሱም ሕዝቡ ዝም ቢል ድንጋዮች እንደሚጮኹ አስታወቃቸው፡፡ ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ሲያያት አለቀሰላት፡፡ “አንቺ ኢየሩሳሌም ለሰላምሽ የሚያስፈልገውን ነገር ምነው አውቀሽ ቢሆን ኖሮ አሁን ግን ይህ ነገር ከዓይንሽ ተሰውሮብሻል ጠላቶችሽ በዙሪያሽ እንደ አጥር ከብበው በዚህም በዚያም አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል… ምክንያቱም እግዚአብሔር ሊያድንሽና ሊጐበኝሽ የመጣበትን ጊዜ ባለማወቅሽ ነው” እያለ ረገማት፡፡
ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ሰለ ደኅንተቷ ሊያሳስባት ፈልጐ ነው፡፡ በማያወላዳ መንገድ ንጉሷና መድኃኒቷ እንደሆነ ገለጸላት፡፡ ወደ ራሷ ተመልሳ ጸጋዋን እንድትቀበል የልቧን ድንዳኔ ትታ እርሱን እንድትሰማ አስጠነጠቃት፡፡ ግን አልተጠነቀቀችም፡፡ ለጊዜው በክብር ተቀበለችው፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ግን ተወችው፤ በመስቀል ላይ ሰቀለችው፡፡ የደኅንነቷን ቀን ማወቅ ተሳናት፡፡ በዚህም ደግሞ ከብዙ ዓመታት በኋላ መዓት ወረደባት፡፡
ይህ የሚያሳዝን የኢየሩሳሌም ሥራ የእኛም ሥራ ነው፡፡ ኢየሱስን መድኃኒታችንን መቀበል አንፈልግም ወይም ተቀብለን በኃጢአታችን ከእኛ እንዲርቅ እናደርገዋለን፡፡ በቅዱስ ቁርባን ወደ እኛ ሲመጣ በደስታ እንቀበለዋለን፡፡ ትንሽ ቆየት ብለን ደግሞ እናዋርደዋለን፡፡ ከእርሱ ጋር እንጣላለን፡፡ ከኃጢአት ጋር ጓደኝነት እንይዛለን፡፡ በኃጢአት ስንወድቅ እርሱን እንደገና እንሰቅለዋለን፡፡ ኢየሱስ እኛን “አቤት በዚህ ቀን ለደኅንነትህ የሚደረገውን ብታውቅ ኖሮ …፣ ይህ ሁሉ ከዓይንህ ተሰውሮብሃል ማወቅን አልፈለግህም፡፡ ይህን እወቅ ግን አንድ ቀን …” እያለ አዝኖ ይፈርድብናል፡፡ ይህንን በማሰብ ሲመጣና ሲናገረን እምቢ አንበለው አናባርረው፡፡ በኋላ እርሱ ቂም ይዞ እምቢ እንዳይለና እንዳያባርረን ደኅንነታችንን ራሳችን አናጥፋት፡፡
ምንጭ:- መንፈሳዊ ማሳሰቢያ - የእለቱ አስተንትኖ