እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዓለምን ሁሉ ከራሱ ጋር ሊቀድስ መጥቷል!

ዓለምን ሁሉ ከራሱ ጋር ሊቀድስ መጥቷል!

photoስለ ክርስትና ስናስብ የጌታ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ የእምነታችን ምሥጢር ቁልፍ ቁም ነገሮች ተደርገው ይታያሉ። ከዚህ አንጻር የጌታ ትሥጉት የመዳን መንገድ መጀመርያ ተደርጎ ስለሚታሰብ እንደ ፋሲካ ምሥጢር ሰፋ ያለ ትኩረት አይሰጠውም። ይልቁንም በዓሉን ቀስ በቀስ ከጌታ ልደት ጋር ብቻ በማያያዝ የሕጻናት በዓል የማድረግ ዝንባሌ ይስተዋላል። ነገር ግን ወልደ እግዚአብሔር “ሰው” ሆነ የሚለውን ምሥጢር ሠርክ አዲስ ማስተዋል እና እርሱን በልብ መያዝ የክርስትና እምነት አስፈላጊ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን አምላክ ሰው ሆነ ማለት ምን ማለት ነው? አምላክ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ጥያቄ የእምነታችንን መሰረታዊ ቁም ነገር የምንመለከትበት ዐቢይ መነጽር ነው። እግዚአብሔር ራሱ ጊዜው በደረሰ ጊዜ ስለ ፍቅር ከእኛ እንደ አንዱ ይሆን ዘንድ ታላቅ እና ረቂቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን መልክ ለብሰን አስቀድመን በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ተፈጥረናል።

እርሱ ከእኛ እንደ አንዱ የሆነው በቀራኒዮ በፈጸመው የማዳን ሥራ፣ በሞቱ እና በትንሣኤው ምሥጢር በኩል የኃጢአት ደመወዝ ከሆነው ከዘላለማዊ ሞት እኛን ለማዳን ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም እርሱ ከእኛ እንደ አንዱ የሆነው ከሁሉ አስቀድሞ፣ ከዘላለም ጀምሮ ለሰው ልጅ ባየው ክብር በኩል እያንዳንዳችንን በእርሱ ክብር ከራሱ ጋር ይቀድሰን ዘንድ ነው። ታላቁ ቅዱስ አጥናቲዎስ “ያልተቀበልነውን ነገር ማዳን እና መቀደስ አንችልም” እያለ እግዚአብሔር የእኛን ማንነት በመካፈሉ ወደ አዲስ የሕይወት ትርጓሜ እና የቅድስና ጽድቅ መውጣታችንን ይመሰክራል። በዚህም አዲስ የቅድስና ሕይወት እግዚአብሔር ራሱ በእኛ ውስጥ ስለ ስሙ ክብር ራሱን ይቀድሳል። በመሆኑም አዲሱ ሰውነት በፍጥረታችን ከአዳም የተካፈልነው አሮጌው ሰውነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በነፍስ እና በሥጋ የተቀደሰው አዲስ ማንንነት ነው። በመሆኑም የቤተ ክርስትያን አበው ይህንን ምሥጢር ሲያብራሩልን እግዚአብሔር ሰው የሆነው ከጸጋ ሥራ የተነሳ ሰው አምላካዊ ይሆን ዘንድ ነው በማለት የጌታን ሥጋ መልበስ ምሥጢር ዓላማ ይገልጹልናል።

እግዚአብሔር አምላክ ምንም እንኳን አዲስ እና ዘላለማዊ፣ ኃጢአትንም ሁሉ ከእኛ የሚያስወግድ ቃልኪዳን ማድረግ ቢቻለውም፤ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከዚህ የተለየ አዲስ መንገድ መርጧል። ይህም አዲስ መንገድ “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” በእግዚአብሔር ሐሳብ ውስጥ የነበረ የሕይወት መንገድ ነው። ይህም የሕይወት መንገድ አንድ ልጁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ጊዜ በሥጋ ተገልጦ ፍጥረትን ሁሉ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከራሱ ጋር ቀድሶ በአባቱ ፊት መልካም መዓዛ ያለው መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት እውነተኛ የሕይወት መንገድ ነው (ዮሐ 14፡6)። በዚህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ሕይወት ውስጥ ሱታፌ አለን። ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ይህንን ሕይወት በሚመለከት እንዲህ ይላል፦

“ ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን” (ኤፌ 1፡4-11)

ቅዱስ ጳውሎስ በእነዚህ ውሱን ቃላት የወልደ እግዚአብሔርን የትሥጉት ምሥጢር አጠቃልሎ ያቀርብልናል። ይህም የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ዘላለማዊ እቅድ ነጸብራቅ ነው። እመቤታችን በምሥጋና መዝሙሯ ውስጥ ይህንኑ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ የማዳን ሥራ እያወደሰች እግዚአብሔርን ስለማዳኑ ታመሰግነዋለች። ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ሲጽፍ ምንም እንኳን በእስር ላይ የነበረ ቢሆንም ቅሉ፤ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ከዘላለም ጀምሮ ለእርሱም ደግሞ ከሁኔታው ባሻገር የሚጠብቀው ዘላለማዊ ተስፋ መኖሩን ያረጋግጥልናል። በመሆኑም የእግዚአብሔር ምርጫ ዓለም ሳይፈጠር በፊት ከዘላለም ጀምሮ የጸና ስለመሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ ምሥክርነቱን ይሰጠናል።

አይሁዳዊ እና የተመረጠው የእሥራኤል ሕዝብ አካል የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር የማዳን እቅድ ሲናገር እግዚአብሔርን የአብርሐም፣ የይስሃቅ እና የያዕቆብ አምላክ ብቻ ብሎ በመግለጽ አያበቃም፤ ይልቁንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እና አምላክ ((ኤፌ 1፡3) እያለ እኛ እያንዳንዳችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም በአብ ልብ ውስጥ እንደታሰብን ያስታውሰናል። እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል “በሰማያዊ በረከት ሁሉ” እያንዳንዳችንን ባርኮናል። ይህም በረከት “በሰማያዊ ሥፍራ” የተሰጠን በረከት ነው።

 ነገር ግን በሰማያዊ ሥፍራ ተባርከናል ማለት ምን ማለት ነው? ይህም ማለት እግዚአብሔር አብ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እያንዳንዳችንን በታላቅ ኃይሉ ትንሳኤ በሰማያት ክርስቶስ ባለበት አድርጎናል ማለት ነው። በሕማሙ እና በሞቱ በኩል ባለን ኅብረት ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ክብር ሱታፌ እንዲኖረን ስለፈቀደ የእርሱ ትንሳኤ የእያንዳንዳችን ትንሳኤ ይሆን ዘንድ በጸጋው ሰጥቶናል፤ በዚህም ከትንሳኤ ክብሩ ሙላት የተነሳ እኛ ሁላችን ከክብር ወደ ክብር እንገለጣለን (2ቆሮ 3፡18)።

በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የላከው መልእክቱ ከቁጥር 4-6 የዚህ ክብር ሁኔታ እንዴት እንደተከናወነ ሲናገር “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” ለዘላለም በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረ፣ ጊዜው በደረሰ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የገለጠው ዘላለማዊ የልቡ ፈቃድ እንደሆነ ይናገራል። ይህ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፈቃድ እያንዳንዳችንን የፍቅሩ ማደርያ የገዛ ራሱ ንብረት የሚያደርገን መለኮታዊ ኃይል ነው። ይህ መለኮታዊ ኃይል የሰው ልጅ የሥራ ደመ ወዝ ሳይሆን ከእግዚአብሔር አብ ልብ የፈለቀ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገለጠ ነጻ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ ሁሉ በእግዚአብሔር አብ ፊት በታትመበት የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ጻዲቅ እና ቅዱስ ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በእግዚአብሔር አብ ፊት ያለንን የልጅነት መብት በሚመለከት እንዲህ እያለ ያስረዳል “ነገር ግን የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው (1ቆሮ 1፡30-31)”። ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ የነበረውን መልክ እና ቅድስና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በአማኞች ላይ ስላደረገ እግዚአብሔር አብ እያንዳንዱን አማኝ በዚሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው የጸጋ መልክ ያውቀዋል። እንደ አማኝ በክርስትያናዊ ሕይወታችን ልንደርስበት የምንችለው ማንኛውም ቁም ነገር ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ሆኖ በአባቱ ፊት ከሚቀርብበት መልክ የሚበልጥ ሊሆን አይችልም። የክብር ተስፋ ያለው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ በመሆኑ (ቆላ 1፡27) በልጁ መልክ በአብ ዘንድ ልጆች ሆነን በፊቱ ለመቆም መብት አግኝተናል። ይህ ሁሉ የሚሆነው “የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ” (ኤፌ 1፡6) ነው። እግዚብሔር አምላክ ከዘላለም ጀምሮ አስቀድሞ እንደመረጠን ስናስብ እንዴት ላለ ታላቅ ክብር እንደተመረጥን ማስተዋል እንችላለን።

ይህ በክርስቶስ ኢየሱስ የተቀደስንበት የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚጠቅለል ነው (ኤፌ 1፡10)። በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እርሱ አሳብ፥ እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ የእግዚአብሔር ጽድቅ ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። በእስር ላይ ሆኖ ይህንን የኤፌሶን መልእክት የሚጽፍልን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምንም እንኳን ወደ እግዚአብሔር ክብር ሙላት ለመድረስ በጉዞ ላይ ብንሆንም ቅሉ የእግዚአብሔር ክብር በመካከላችን መገለጡን እና እኛም የዚህ ክብር ተካፋዮች መሆናችንን በእምነት ያረጋግጥልናል። በመሆኑም በሰማይ እና በምድር እንደሚኖር አማኝ በአሁናዊው፣ በመካከላችን “አማኑኤል” በሆነው እና በሚመጣው የእግዚአብሔር ክብር በሁለቱም ባለድርሻ ነን።

ከዚህም የተነሳ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ቤተ ልሔም ወይም የእኛን ምድር ብቻ የሚመለከት ቁም ነገር ሳይሆን ዓለምን እና ሞላዋን የሚመለከት የአዲስ ፍጥረት ልደት ነው። ዓለም ሁሉ የተፈጠረበት የእግዚአብሔር ቃል፣ ሁሉ በእርሱ፣ ለእርሱ እና ከእርሱ በመሆኑ ልደቱ ሁሉን ነገር ከእርሱ፣ በእርሱ ለእርሱ የሚቀድስ እና በአባቱ ፊት  እንከን የሌለበት አድርጎ የሚያቀርብ በጸሎተ ሃይማኖታችን እንደምንታመነው “ሁሉ በእርሱ የሆነ! ያለ እርሱ በሰማይም በምድርም ምንም ያልሆነ” የእግዚአብሔር መገለጥ ነው። ይህ በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነ የእግዚአብሔር መገለጥ ከዘላለም ጀምሮ በእግዚአብሔር አብ ልብ ውስጥ የታሰብንበት ሐሳብ፣ የተፈቀርንበት ፍቅር፣ ወደ ሕይወት የተጠራንበት ቃል እና የተፈጠርንበት መልክ ነው። እርሱ በእኛ ከዘላለም ጀምሮ በአባቱ የታወቀበትን መልክ ስላኖረ ጊዜው በደረሰ ጊዜ ይህ የእግዚአብሔር መልክ በመካከላችን ተገለጠ። በዚህም የተፈጠርንበትን ክብር እናውቅ እና የእርሱን መልክ በማየት የራሳችንን መልክ እናስተውል ዘንድ፣ በዚህም ከክብራችን እና ከተፈጠርንበት መልክ ጋር የማይዛመድ ባዕድ መልክ ከእኛ ወዲያ እናስወግድ ዘንድ ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቷል!” (ዮሐ 14፡9) በማለት የመልካችንን የክብር ጥግ ያሳየናል።

እግዚአብሔር አምላክ ለአሮን እና ለካህናት ሕዝቡን የሚባርኩበትን ቃል ሲሰጣቸው “እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ” እያለ የሰውን ልጅ ሕይወት በሁለንተናው ለበረከት የሚያደርግ ቃል ይናገራል(ዘኁ 6፡24-26)። ይህ የጌታ ልደት የእግዚአብሔርን ፊት የምናይበት፣ የእግአብሔርን መልክ በማስተዋል ራሳችንን በእግዚአብሔር ክብር የምንመለከትበት እና የምንቀበልበት፣ ብሎም ወንድሞቻችንን በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ መልክ የምናይበት፣ የምናውቅበት እና የምንቀበልበት፣ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ እያንዳንዳችን እና ወደ ሀገራችን የሚመልስበት፣ ሰላም በሰው ልጆች መካከል ቅንጦት የማይሆንበት እና ለዚህም ሁሉ የምንታዘዝበት ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!

መልካም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል!

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት