እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የአዲስ ዓመት ተስፋችንና ምኞታችን እንደ ቤተሰብ ምን ላይ ያተኩር?

የአዲስ ዓመት ተስፋችንና ምኞታችን እንደ ቤተሰብ ምን ላይ ያተኩር?

1አዲስ ያልነው ዓመት የማይክሮ ሰኬንድ፣ የሰኬንድ፣ የደቂቃ፣ የሰዓታት፣ የቀናት፣ የሳምንታትና የወራት አቆጣጠር ቅብብሎሹን ሳያዛንፍ እያሸጋገረ ይሄድና “አሮጌ ዓመት” ወደሚባለው ጥግ ይደርሳል፡፡ ተፈጥሮአዊው ሂደትና ልማዳዊው መስተጋብር ይዛመዱና “አዲስ ዓመት” ወደሚለው ተስፋና ምኞት ያሻግረናል፡፡ “አዲስ” የሚለውም እሳቤ ከነበረውና ከተለመደው ነገር፣ ቁስና አካሄድ ወጣ ብሎ የተለየ ነገር ወደ ማሰብና ማቀድ ያደርሰናል፡፡ ይህ ነው ሕይወትን ከአሰልችነት አውጥቶ በተስፋና በምኞት የተሞላ የሚያደርገው፣ ለሌሎችም በጎነትን ለማጋራት የሚያነሳሳው፡፡ ይህንንም ተንተርሰን በጊዜ ቀመር ልምዳችን “አዲስ ዓመት”ን እናስባለን፣ እንመኛለን፣ ለተሻለ ነገር፣ ለበጎው ነገ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ውስንነቶች ካሉንም ውስንነቶቻችንን ለማቃናትና ለማስተካከል ቁርጥ ፈቃድ እናደርጋለን፡፡

እንደቤተሰብ እነዚህን ተስፋዎቻችንንና ምኞቶቻችንን ይዘን ነው ወደ “አዲስ ዓመት” ለመሸጋገር የምንደረደረው፡፡ ይሆንልን ዘንድ ባሰብነው መጠን እያሰላን ለርስበርሳችን የ“አዲስ ዓመት” መልካም ምኞት እንለዋወጣለን፡፡ ያሳለፍነው ዓመትና ያለንበት ዘመን ምንም እንኳን በበጎነት የማናወድሰው ቢሆንም (በአብዛኛው በሰው-ሠራሽ ችግሮቻችን ምክንያት) በሕይወትና በጤና ሆነን ወደዚህ ጊዜ ለመድረሳችን አምላካችንን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡ ሰቆቃወ ኤርምያስ እንደሚያስገነዝበን: “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሣ ነው፣ ርህራሄው አያልቅምና፡፡ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፡፡”(3፡22-23) ያለውን ይዘን የትላንት ጊዜያችንንና ያሳለፍነውን ዓመት ዞር ብለን ስናስብ ለዛሬ መድረሳችን በኛ ጥንቃቄና መልካምነት ብቻ ሳይሆን በርሱ ምህረትና ፈቃድ መሆኑን አንዘነጋም፡፡ ይህም ለማመስገናችን ምክንያት ይሆነናል፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ያዕቆብ: “መልካም ሥጦታ ሁሉ፣ ፍጹምም በረከት ሁሉ፣ እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከላይ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡”(1:17) ያለውን እናምናለንና፡፡

ማመስገናችን የኛን መልካምነት ለማሳየት ወይም በነበርንበት ለመቀጠል ሳይሆን በአዲስ ተስፋና ምኞት ተነቃቅተን ለመጓዝ፣ ለመኖርና ለማገልገል ሊሆን ይገባል፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ፡ “እነሆ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፣ እርሱም አሁን ይበቅላል፡፡”(43:19) ያለው አምላክ ዛሬም ለያንዳንዳችን እንደ ግለ-ሰብ፣ እንደቤተሰብ፣ እንደ ተስፈኛ ክርስቲያን ስለ አዲስ ዓመት ተስፋችንና ምኞታችን ስናስብ እርሱ የሚለንንም አስተውለን እንያዝ፣ እንመርኮዘውም፡፡ አምላካችን ቀድሞ እንደተናገረው፡ ዛሬም ለያንዳንዳችን፡ “ለእናንተ የማስበውን አሳብ እኔ ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ ለወደፊት የሠመረ ጊዜና ተስፋ ልሰጣችሁ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም፡፡”(ኤር.29፡11) በማለት ተስፋችንን ያለመልመዋል፡፡

እርሱ ይህን ካለን እኛስ በአዲስ ዓመት በምን ላይ እናተኩር? ምንን ለማጠናከር ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ? ምን ይዘንስ በሚሰጠን (በተሰጠን) ዓመት በፊቱ እንመላለስ? አንባቢያን ሁላችን የየራሳችን የተለያየ የትኩረት አቅጣጫና የተስፋ መንገድ ሊኖረን እንደሚችል ተገማች ቢሆንም፡ Matthew Kelly የተባለ ጸሐፊ The Four Signs of a Dynamic Catholic (በግርድፉ ሲተረጎም አራቱ የንቁና ትጉ ካቶሊክ መለያዎች) በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ያሰመረባቸውን አራት የንቁና የትጉ ካቶሊክ መለያዎች እኛም የዓመቱ የየግልና የቤተሰብ ትኩረቶቻችን ብናደርጋቸው መልካም ሆኖ ታየኝ፡፡ እነርሱም 1. ጸሎት፣ 2. ንባብ፣ 3. በጎ ተግባርና 4. የምስክርነት ሕይወትን ማጠናከርና መኖር፡፡ እነርሱንም በአጭሩ እንይ፡፡  

1. ጸሎት

በካቶሊካዊ አስተምህሮ ጸሎት “አእምሮአችንንና ልባችንን ወደ አምላካችን የምናነሳበት ወይም በጎ ነገሮችን ከአምላካችን የምንጠይቅበት” ዋነኛ መንገድ ነው፡፡ ይህም የካቶሊካዊነታችን ዋና መገለጫ ነው፡፡ እንደ መታደል ሆኖ ካቶሊካዊ የጸሎት አደራረጋችን በእጅጉ የበለጸገና በተለያየ መልኩና ጊዜ መከናወን የሚችል ነው (በዚህ ዝርዝር ጉዳይ ላይ ወደ ፊት እንመለስበት)፡፡ በግልም ሆነ፣ በቤተሰብ፣ በቡድንም ሆነ በማኅበር ጸሎት ለማድረስም ሆነ ለመሳተፍ በእጅጉ ምቹ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተለያዩ ምክንያቶችና ባሉብን የአኗኗር ጫናና ኑሮን ለማሸነፍ ከምናደርገው ሩጫ የተነሣ የጸሎት ልምዳችን እየተሸረሸረ ያለ ይመስላል፡፡ አንዳንዴም ጸሎታችን የይስሙላና ወግ ማድረሻ ሲሆንም ይስተዋላል፡፡ በዚህ ዓይነት የጸሎት መዳከም መንገድ ላይ በግልም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ያለን ካለን፡ ሐዋርያው ያዕቆብ፡ “ስለማትጸልዩም የምትፈልጉትን ነገር አታገኙም፡፡ ብትጸልዩም የጸሎታችሁን መልስ የማታገኙት የለመዳችሁትን ነገር በሥጋዊ ደስታ ላይ ለማዋል በክፉ ሐሳብ ስለምትጸልዩ ነው፡፡”(4፡2-3) እያለ የሚያስጠነቅቀንን በማሰብ የጸሎት አደራረጋችንን፣ ልምዳችንንና የትጋት አቅጣጫችንን በ“አዲስ” ዓመት ለማቃናት ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ፡፡

ማቲው ኬሊ እንደሚለው በጸሎት የሚተጋ፣ ከዕለታዊ ተደጋጋሚ ተግባራቱ ይልቅ ጸሎትን መደጋገም ቀዳሚ ተግባሩ ያደረገ ንቁና ትጉ ካቶሊክ ግለሰብም ሆነ ቤተሰብ “መንፈሳዊ ጤንነት ስለሚሰማው ምንም ነገር ሊያሳስበውና ሊያውከው” አይችልም፡፡

2. ንባብ

መጽሐፍ ቅዱሳችን፣ ታላቁ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትምህርተ-ክርስቶስ፣ የቤተክርስቲያን አባቶች የተለያዩ ዘመናትና ወቅታዊ ድንጋጌዎች፣ የቅዱሳን ገድለ-ታሪኮችና ሌሎችም በየጊዜው ወቅቱን ጠብቀው የሚወጡ መንፈሳዊ ጽሁፎች ከተጠቀምንባቸው ካቶሊካዊ የንባብ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡ ካቶሊካዊ ማንነታችንንም መገንቢያ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በግልም ሆነ በቤተሰብ እነዚህን ጽሑፎች የማንበብን ልምድ ማዳበር እንደ ማቲው ኬሊ አገላለጽ “በቅድስና ለማደግ” ወይም “የራሳችን የተሻለ ግልባጭ” ለመሆን የሚረዳን መንገድ ነው፡፡ ዘመናችን “እውነት የሌለው ዓለም፡ ደስታ የራቀውና ትርጉም የጠፋበት” እንደ ሆነ ማቲው ኬሊ አስምሮበታል፡፡ እኛም በዘመናችን እያየንና እያስተዋልን ያለነው የሀሰት መረጃ፣ እየተነዙ ያሉ ውጫዊ ስሜት አማላይ ጹሁፎች፡ ሰዎች በቅድስና ከማደግ መንገድ ማፈንገጫ መስመራቸውን ማሳያ እንደሆነና በዚህም ለሌላው ተስፋና ብርሃን ከመሆን ይልቅ የሌላውን አበሳና ስቃይ ማባዣ ሲሆኑ እናስተውላለን፡፡

እንደ ማቲው ኬሊ አገላለጽ “ንቁና ትጉ ካቶሊክ በግሉም ሆነ በቤተሰብ በየቀኑ ስለ እምነቱና ስለቤተክርስቲያኑ እያነበበ የኢየሱስና የቤተክርስቲያኑ ተማሪ ሆኖ [ዕድሜውን ሙሉ] በቅድስና ያድጋል፡፡” አንተስ/አንቺስ ይህን የንባብ ምርኩዝ ለማንሳትና በመጪው ዓመት “ንቁና ትጉ ካቶሊክ” ሆኖ ለማደግ ንባብን በተመለከተ ምን አስበሃል?  

3. በጎ ተግባር

እግዚአብሔር በብዙ መልኩ ለፍጥረታቱ ሁሉ ያለ ማዳላት ቸርና ለጋስ እንደሆነ እናውቃልን፡፡ በመሆኑም ለጋስነትና በጎ ተግባር የክርስቲያን ሕይወት ማዕከል ነው፡፡ ሆኖም ግን ራስ-ወዳድነት እየተንሰራፋ ባለበት ዘመን ለምንኖር ካቶሊካውያን ግለሰቦችም ሆን ቤተሰቦች የለጋስነት በጎ ተግባራችንን እንዴት እንለካዋለን? እያደገ ነው? ወይስ እየቀጨጨ? የለጋስነት በጎ ተግባር በተለያየ መልኩ ይከናወናል፡ በገንዘብ፣ በዕውቀት፣ በጊዜ፣ በሀሳብ፣ በማንነት፡፡

የአዲስ ዓመት ተስፋችንንና ቁርጠኝነታችንን ስናስብ “አምና ካበረከትሁት የለጋስነት በጎ ተግባር፣ ለሌሎች በጎነትም ይሁን ለቤተክርስቲያን ዕድገትና መሻሻል ዘንድሮ በምን ያህል ማሳደግ አለብኝ?” የሚለውን ጥያቄ አንስተን ምላሹን መቁረጥ አለብን፡፡ የለጋስነታችን በጎ ተግባር ለሌሎችም ሆነ ለቤተክርስቲያን ባለን ማንኛውም መልኩ ሊሆን ይችላል፡፡ ልብ ማለት ያለብን፡ “ይህን አስታውሱ፣ በጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራም ብዙ ያጭዳል፡፡ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና፣ እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበው ይስጥ፡፡”(2 ቆሮ.9፡6-8) የሚለውንና “በልግስና የሚሰጥ ሰው አለ፣ ይጨመርለታልም፡፡ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፣ ይደኸያልም፡፡”(ምሳ.11፡24) የሚለውን የቃሉን ምሪት ነው፡፡

እንደ ማቲው ኬሊ አገላለጽ ሦስተኛው የንቁና የትጉ ካቶሊክ መገለጫው የለጋስነትን በጎ ተግባር የማሳደግ አቅሙ ነውና በአዲስ ዓመት የዘመኑ አቆጣጠርም ሆነ የዕድሜያችን ቁጥር በሚጨምረው መንገድ፣ ከላይ በተሰጠንም መጠን፡ ምን ያህል የለጋስነት በጎ ተግባር ለመጨመር እንቁረጥ?  

4. የምስክርነት ሕይወት

እንደ ማቲው ኬሊ አገላለጽ አራተኛው የንቁና የትጉ ካቶሊክ መገለጫ የምስክርነት ሕይወቱ ነው፡፡ ማቲው ኬሊ “ዓለማችን ያለማቋረጥ በበጎውም ሆነ በክፉው እየተለወጠች ትገኛለች፡፡ በበጎውም ሆነ በክፉው የመለወጧ ሁኔታ እኛ ዛሬ ላይ ባለን የአኗኗርና የአስተሳሰብ መንገድ ነው፡፡ እስቲ አስቡ! የሚከሰቱ ክፉ ነገሮችን ሁሉ በአሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ባሉ ሕይወት-ሰጪ ጥበብ ብንኖር ኖሮ ምንኛ በበጎነት በለወጥናቸው ነበር፡፡” ይላል፡፡ ዛሬ በዓይናችን ሥርና በየቤታችን፣ በየሰፈራችንና በየሥራ ሥፍራችን እየተከሰተ የሚስተዋለው ማንኛውም ክፉ ነገር ከምስክርነት ሕይወት ጉድለት ለመሆኑ ስንቶቻችን ልብ ብለናል፡፡ ባንድ ወቅት አንድ አባት ሲያስተምሩ “98.6% አብርሃማዊ እምነት [ክርስቲያን፣ እስላምና ይሁዲ] ተከታይ አለባት በምትባል ሀገር [ኢትዮጵያ] ክፋት ለምን በዛ?” ብለው ያነሱትን ጥያቄ በጠብታ ለመመለስ ዛሬ “ንቁና ትጉ ካቶሊክ እሆናለሁ፡፡” የምንል ወገኖች በአዲስ ዓመት የምስክርነት ሕይወታችንን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንነሳ፡፡  

ስናጠቃልልም በአዲስ ዓመት ማድረግና መሆን በምንፈልገው ተስፋችንና ምኞታችን፡ ትኩረታችን እነዚህን አራት የ“ንቁና ትጉ ካቶሊክ” መለያዎችን ከፍ አድርገን በመያዝ እኛም የነዚህ የ“ንቁና ትጉ ካቶሊክ” ሰልፈኞች አካል ሆነን ለመዝለቅ ይህንን ጸሎት ምርኩዛችን እናድርገው፡፡ “የጊዜያት ሁሉ አምላካችን ሆይ! ወደ ‘አዲሱ’ ዓመት በጥሞና እንድንሻገር እርዳን፡፡ ስለራሳችንና ስለሌሎች ማንነት አሳቢዎች፣ እያንዳንዷ ዕለታዊ እርምጃችን በጎ ትርጉም ያላት፣ ቃላችንም የበጎነት አቅም ያለው ይሆን ዘንድ አብቃን፡፡ ፍጥረታትን ሁሉ ተንከባካቢዎች እንጂ አጥፊዎች እንዳንሆን ጠብቀን፡፡ የነፍሳት ሁሉ አፍቃሪ አምላክ! ወደ ‘አዲሱ’ ዓመት በደስታ በመግባት በሚኖረን ቁርጠኝነትና ተስፋ በጎነትን በቤተሰባችንም ሆነ በሁሉም መስክ በማጋራት የማንነታችንን መለያ አጥብቀን የምንይዝና የምንኖርበት፡ በምንሰጠው መጠን ካንተ በረከትን ለመቀበል የምንዘጋጅ ልጆችህ አድርገን፡፡ አሜን፡፡” መልካም አዲስ ዓመት፡፡ (አርጋው ፋንቱ)

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት