እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሁለት የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ወደ ቤተልሔም ዋሻ ሲገቡ!

ሁለት የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ወደ ቤተልሔም ዋሻ ሲገቡ!

the Cave of Bethlehemአንድ እኔ ሁሉን አዋቂ ነኝ፤ አለሁ አለሁ የሚል ትእቢተኛ እና አንድ ትሑት፤ ሁሉንም ነገር እንደማያውቅ የሚያውቅ።

የመጀመሪያው ሁሉን አውቃለሁ የሚለው ዕቡይ ሰው ኢየሱስ ወደ ተወለደበት ዋሻ ገባ። መግቢያዋም አጠር ያለች ናትና ሰውዬው ውስጡ ካለው ትእቢት የተነሣ ጎንበስ ማለቱን ባይወደውም እንደምንም አጎንብሶ ወደ ቤተልሔሙ ዋሻ ውስጥ ገባ። ይህን መሰሉ ታላቅ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ሲገባ በዚያ ዋሻ ታላቁን እግዚአብሔር ያገኘዋል ብሎ ማሰቡ ይከብዳል፤ ምክንያቱም እኔ ትልቅ ነኝ ብሎ ራሱን የደረጃዎች ጫፍ ላይ ቁጭ ያደረገ ሰው ከርሱ በላይ ታላቅ የሚባል ያለ አይመስለውም። እኔ ጠቢብ ነኝ ብሎም ያስባልና ከርሱ የሚበልጥ የጥበብ ባለቤትም መቀበል አይችልም፤ እኔ ከሌሎች የሚያስፈልገኝ የለም ብሎ ስለሚያስብ እግዚአብሔርን ማግኘቱ ምንም አይጨምርለትም፤ እናም በዋሻው ውስጥ ሕፃኑን ቢያየውም እግዚአብሔርን ማየት ይከብደዋል። ይህ ሰው ስለራሱ ሲያስብ ታላቅ ራሱ ስለሆነ ሌሎች ሁሉ ከርሱ ያነሱ ናቸው።

ለዚህ ዕቡይ ሰው ይህ በብጣቂ ጨርቅ የተጠቀለለው ሕፃን ከመላው ዓለም የገዘፈ ነው ብሎ ማሰብ አይታሰብም፤ በግርግም ላይ የተኛው አንድ ክንድ የማይሞላ ሚጢጢ ጨቅላ ለሰውዬው የነገሥታት ንጉሥ ሊሆን አይችልም። ለእርሱ ይህ ከመወራጨትና ከማልቀስ በቀር አንዲት ቃል እንኳ ማውጣት የማይችል ሕፃን የዘላለማዊ ጥበብ ባለቤት ሊሆን አይችልም።

የዓለም አዳኝ ተወልዶላችኋል ሂዱና እዩ ተብለው መላእክት ያላቸውን ሰምተው አምነው የመጡትን እረኞች ባየ ጊዜ ዕቡዩ ሰውዬ በንቀት ፈገግ ብሎ ተመለከታቸው፤ የእረኞቹስ ብዙም አይደንቅም ደህና ብሎ አሰበ፤ ግን እነዚህ “ሦስቱ ጠቢባን” እንደ ሞኝ አምላክ በኮከብ መራን ብለው ይህች ደሳሳ ዋሻ ድረስ ከሩቅ መገስገሳቸው ገርሞት “አይ አላዋቂነት!” አለ በውስጡ።

ጠቢባኑን ታዝቦና ንቆ ሲያበቃ በዓይኑ ሲያማትር ወደ ድንግል እናት ቅ. ማርያም ተመለከተ። አልግረመውም፤ አልተደነቀምምም ለርሱ እርሷ ማንም ናት፤ ከራሱ እናትም እጅግ ዝቅ ያለች! “ያልታደለች ድኻ!” አለ በውስጡ፤ ድኻ ሆና ደግሞ መውለዷ! በአእምሮው ጽንስ መከላከያን አሰበና ይህን ባታውቅ ነው እንጂ በዚህ ድህነቷ ባልወደለችም ብሎ በርሱ እውቀት ልክ ደመደመ። ኋላ ቀር ዓይነት እናት መሆኗን ለራሱ አሳመነና ይህን መሰል ሕፃን የሰማይና የምድር ፈጣሪ ብሎ ባለማመኑም የሚያውቃቸውን ሳይንሶች በአእምሮው እያጣቀሰ አመሰገነ።

ሰውዬው ለአንድ ሁለት ደቂቃ ካሰመጠው የሃስብ ትርምስ ሲባንን ቅ. ዮሴፍን ከእመቤታችን አጠገብ ደስ ብሎት ሕፃኑን ሲመለከት አስተዋለ፤ ገርመም አድርጎ አየውና “ይሄ መናጢ አናጢ! እውነትም ማደሪያ ከልክለውት መንከራተቱ ሲያንሰው ነው!” ብሎ ዮሴፍ ላይ ዕቡዩ ሰው በውስጡ ችሎት ፈረደ።

ትእቢተኛው ሰው “እዚህ ዋሻ ውስጥ ከዚህ በላይ መቆየት ትርጉም የለውም…የባከነ ጊዜና ድካም ነው ቆይታዬ፤ ሰዎቹም ሆነ ቦታው አይመጥነኝም” ብሎ አሰበና ሰዎችም በዚያ ካዩት ትዝብት ውስጥ እንዳይገባ በመጣደፍ ቅድስት ቤተሰብን በዚያ ትቶ ወደራሱ አቅጣጫ አመራ።

በትእቢቱ ምክንያት ሰውዬው ወሰን የሌለው ፈጣሪውን ማወቅና ማግኘት አቃተው፤ ትልቅ ነኝ ብሎም ስለሚያስብ ትንሽ ሆኖ የመጣውን አምላክ እንደ ትልቅ መቀበል አልቻለም። ከኛ በላይ የሆነን ትልቅ ነገር እንደ ትልቅ መቀበል የምንችለው ትንሽነታችንን መቀበል ስንችል ብቻ ነው።

“ከነዚህ ሕፃናት እንደ አንዱ ካልሆናችሁ በስተቀር ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት አትችሉም” አለ ክርስቶስ።  

አሁን ወደዛች የቤተልሔም ደሳሳ ዋሻ የሚገባው ሁሉን ነገሮች እንደማያውቅ የሚያውቅ ግን የማያውቀውን ለማወቅ ዝግጁ የሆኑ ትሑት ሰው ነው። ልክ ያ ትእቢተኛው ሰውዬ ሲያይ የነበረውን ነገሮችና ሰዎች ሁሉ ተመለከተ፤ ሆኖም ግን ልዩ ሆነው ይታዩት ነበር።

ትሑቱ ሰው ከታች ወደላይ ከግርግሙ በላይ ያለውን የዋሻውን ጣራ ሲመለከት እጅግ የገዘፈ የከዋክብት አጎበር ይመለከታል፤ ሰማያዊውን ውበት ለማየት የዋሻው ጣራ አልገደበውም። ሕፃኑን ተመለከተና ምድርም ሰማይም ሊሸከሙት የማይችል አምልክ መሆኑን አስተዋለ፤ ይህ ሕፃን በግርግም መተኛቱን አየና እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ምግብ ሊሆን መምጣቱን ተረዳ። ለዚህ ሰው የዚያ ውብ ሕፃን ብርሃን ፈንጣቂ ዓይኖች የሰውን ልብ የማየትና ድብቅ ሃሳቦችን የመመርመር ብቃት አላቸው።

ለዚህ ሕፃን ሙቀትን ብሎም ሕይወትን ለመስጠት የተጠቀለሉ ጨርቆችን ትሑቱ ሰው በጥልቀት ባስተነተነ ጊዜ ይህ ሕፃን ወሰን የለሽ መሆኑንና በመግነዝ ጊዜ በመግነዝ ጊዜም ተፈተው እንደሚወረወሩ አሰበ፤ ምክንያቱም ሕይወት ሰጪው እሱ በጨርቅ ሊታሰር አይቻልምና! የሕፃኑ ትናንሽና ቀይ ከንፈሮች ለአላዛርና ለብዙዎች ከመቃብር መውጣትን የሚያውጁ፤ ዛሬ ቃላት ማውጣት ያልቻለው የዚህ ሕፃን አንደበትም ድዳዎችን የሚፈታ የዓይነ ስውሮችን ዓይን የሚከፍት፤ በልምሻ የታሰረን የሚያስቦርቅ ነው። አዎን አለ ትሑቱ ሰው እነዚህ ከናፍር የሰላምና የእርቅ መልክትን ለዓለም ያበስራሉ።

ትሑቱ ሰው የሕፃኑን ትናንሽ እጆች አስተዋለና የነዚህን እጆች ግዝፈትና ስፋት አሰበ፤ እነዚህ እጆች የዓለምን ሕዝብ በሙሉ ልክ በሚዛን ላይ እንደተሰፈረ እህል ሰፍረው የያዙ ናቸው አለ። ሕፃኑ ያረፈበት የከብት ግርግም በላዩ ላይ ንጉሥ ተኝቶበታልና ዙፋን ሆኖ ታየው፤ ዋሻዋም ደሳሳነቷ አልታየችውም ሰውዬው ውብ ቤተ መንግሥት ውስጥ የገባ መስሎታል።

የሕፃኑን እናት ካስተዋለ በኋላ እግዚአብሔር የተናግረውን እንደሚፈጽም ማመኗና መታዘዟ ደስ ብሎት በእርሷ ይሁንታ ይህ ሕፃን ለብዙዎች መድኅን ሊሆን መወለዱን አስቦ “ምንኛ ጸጋን ተሞልሽ!” አለ በልቡ። “ደግሞስ እኔ ከርሷ ጋር በዚህ መገኘቴ እንዴት የታደልኩ ነኝ!” አለ ለራሱ። “እጮኛዋስ እንዴት ያለ ጻድቅ ቢሆን ነው ለዚህ ኃላፊነት የተመረጠው! የእግዚአብሔር ልጅ ይወለድና እንደ ሰው ያድግ ዘንድ አጋዥ ከመሆን በላይ ሀብትና ርካታ ምን አለ?”። ድንቅ ሕፃን እናትና አባት፤ እውነትም ቅድስት ቤተሰብ!

ትሑቱ ሰው ሕፃኑ ወተትን እንደሚጠባ ቢያይም ይህ አምላክ የሰማይ ወፎችን የሚመግብ መሆኑን ያውቃል፤ ከቅድስት እናቱ እንደ ሥጋ ቢወለድም ከእርሷ አስቀድሞ ይኖር የነበረ መሆኑንና ከዚህም የተንሣ ቅድስት እናቱን እንከንና እድፍ የለሽ ውብ አድርጎ እንደፈጠራት ያምናል።

አላዋቂነቱን ስለሚያውቅ ትሑቱ ሰው ከሕፃኑ የጥበብ ጌታ ጥበብን ሸመተ። ደካማነቱን ይታመናልና ከኃያሉ አምላክ ኃይልን አገኘ። በርግጥም ትሑት መሆኑ ታላቅና ወሰን የለሽ የሆነውን አምላክ እንደ አምላክነቱ እንዲቀበል አስችሎታል ምክንያቱም ከኛ በላይ የሆነን ትልቅ ነገር እንደ ትልቅ መቀበል የምንችለው ትንሽነታችንን መቀበል ስንችል ብቻ ነው።

አዎን፤ ርዳታና ጸጋ እንደሚያስፈልገው የሚረዳ ሰው ትሑት መሆን ይኖርበታል፤ በዚህም ምክንያት የጌታችን ልደትን መረዳት ስንሻ ስለእምነታችን ከምናያቸው ነገሮች ማዶ መሄድ መቻል አለብን። አእምሯችን ሊያግዘንና ከነገሮች ወዲያ ሊያሻግረን እንጂ በምናየው ነገር ብቻ ሊገድበን አልተፈጠረልንም። በገና ጊዜ የምናስበው ሕፃኑ ክርስቶስ ከከዋክብት በታች በርቀት ዝቅ ብሎ እኛ የቆምንበት አፈር ላይ ቢተኛም እርሱ ራሱ ከዋክብትን የዘረጋ ፈጣሪ መሆኑን እምነታችን ይነግረናል። ለዚህ ከፍ ላለው አምላክ በትሕትና ክርስትናችንን ከሰው ልጆች ጋር በሰላምና በፍቅር በመኖር የሚገባውን ክብር እንግለጽለት።  

ቡሩክ ልደተ ክርስቶስ!

ከ F.J. Sheen “The Eternal Galilean” pp. 12-15 የተወሰደና የተዋሐደ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት