ጰራቅሊጦስ
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Saturday, 11 June 2011 20:13
- Written by Super User
- Hits: 4425
- 11 Jun
ጰራቅሊጦስ
ሐዋርያት ኢየሱስ እንደሚተዋቸው ሲያውቁ አዘኑ፡፡ ኢየሱስ ግን “እሄዳለሁ ስላልኋችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞላ ነገር ግን እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፡፡ ካልሄድኩ መንፈሰ ቅዱስ አይመጣላችሁም፡፡ ከሄድኩ ግን እልክላችኋለሁ” ዮሐ. 16፡6 “መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ እውነትን ሁሉ ያስተምራችኋል” የሐዋ. 16፡13 “አባቴ ከእናንተ ጋር ለዘወትር የሚኖር አጽናኝ እንዲልክላችሁ እለምነዋለሁ” ዮሐ. 14፡15 “ከላይ የሚወርድ ኃይል መንፈስ ቅዱስ እስክትቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ሉቃ. 24፡49 እያለ አበረታታቸው፡፡
እነርሱም ቃሉን አምነው ከእመቤታችን ማርያምና ከሌሎች ሴቶች ጋር በጽዮን አዳራሽ በጸሎት ተጠመዱ፡፡{jathumbnail off} በዚህም ሁኔታ ሲጠብቁት ሳለ ነፋስ የሚመስል ድምፅ ያሉበትን ቤት ሞላው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ፡፡ በራሳቸውም ላይ የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ነጸብራቆች ታዩአቸው፡፡ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ በተለያዩ ቋንቋዎችም መናገር ጀመሩ፡፡ የሐዋ 1፡12፤2፣1-14
“ከላይ ኃይል እስኪሰጣቸው ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ብሎ ኢየሱስ ያዘዛቸው ይህን ሰማያዊ ኃይል ካልተቀበሉ ሐዋርያት እውነተኛ ተከታዮች ስለማይሆኑ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላቸው ኖሮ ኢየሱስ የሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት እክል ሲያጋጥማቸው በፈሩ፣ በርግገውም ኢየሱስን ትተውት በተበታተኑ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፡፡ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ ሀገር ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” እያለ ተንብዮላቸው ነበር፡፡ የሐዋ. 1፡8 ትንቢቱ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ተፈጸመ፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ሲወርድባቸው በመለወጣቸው መንፈሳዊ ሐሳብ አደረባቸው፤ ካለ ኢየሱስ በስተቀር ስለ ሌላ አይናገሩም፣ አያስቡም ነበር፡፡ በመጀመሪያ የነበራቸው ፍርሃት ጥርጣሬ ተወግዶ መንፈሳቸው ጽናትን አገኘ፣ እምነትና ብርታት ሞላባቸው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለብሰው ስለ ክርስቶስ በሁሉ ቦታ በግልጽ ሲሰብኩ፣ ለሰው ደኅንነትን ማብሰር ጀመሩ፡፡ ስብከታቸው ደግሞ ብዙ ፍሬ አፈራ፡፡ ነፍሳት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሳባቸው፡፡
እኛም ደግሞ በጥምቀት በሜሮን መንፈስ ቅዱስን ተቀብለናል፡፡ በእኛ ላይ ወርዶ ከኃጢአት ልጅነት የጽድቅ ልጆች አደረገን፡፡ ከእኛ ጋር አለ፣ ይመራናልም፡፡ በጸጋው አእምሮአችንን ያበራልናል ምኞታችንን ያሳካልናል፡፡ ሐዋርያት በጥሩ ዝግጅት ተቀብለውት እኛ ግን በቀዘቀዘ መንፈስ እንቀበለው ይሆን? በሐዋርያት ላይ ሲወርድ የቅድስና ፍሬ አሳየ፤ በእኛ ላይ ግን በበደላችን ምክንያት ያለ ቅድስና ፍሬ ይቀራል፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የግድ ያስፈልገናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣልን ተዘጋጅተን በልባችን እንቀበለው፡፡ በደንብ እናዳምጠው፡፡ በሙሉ ልባችን እንታዘዘው እናክብረው፡፡ በኃጢአታችን ከእኛ እንዳናርቀው እንጠንቀቅ፡፡
ምንጭ፡ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ